አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ለአርቲስት እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) የክብር ዶክትሬት ሊሰጣት መወሰኑን አስታወቀ፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ጋርዳቸው ወርቁ (ዶ/ር) እንደገለጹት÷ ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ ዘርፎች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ሐምሌ 13 ቀን 2015 ዓ.ም ያስመርቃል፡፡
በዕለቱም ለተወዳጇ አርቲስት እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) የክብር ዶክትሬት ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ነው ያረጋገጡት፡፡
ድምፃዊት፣ ገጣሚ፣ የዜማ ደራሲ እና ተዋናይት የሆነችው ሁለገቧ አርቲስት ጂጂ፥ የሀገሯን ባህልና ሙዚቃ ለዓለም በማስተዋወቅ ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫውታለች ብለዋል ፕሬዚዳንቱ፡፡
በተጨማሪም በኪነ-ጥበብ ሥራወቿ÷ የአዊን ሕዝብ ቋንቋ እና ባሕል በማሳደግ ላበረከተችው አስተዋፅኦ የክብር ዶክትሬቱ ይበረከትላታል ማለታቸውን የዩኒቨርሲቲው መረጃ ያመላክታል፡፡
ለጂጂ የሚሰጠውን የክብር ዶክትሬት እና የተማሪዎቹን የምርቃት ሥነ- ሥርዓት በማስመልከት የፊታችን ሐምሌ 12 ቀን 2015 ዓ.ም ከቀኑ 8:00 ለመገናኛ ብዙኃን ዝርዝር መግለጫ እንደሚሰጥ ጠቁመዋል፡፡