አዲስ አበባ፣ ሐምሌ7 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐረሪ ክልል በተጠናቀቀው የበጀት አመት ከ1 ቢሊየን 746 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የክልሉ ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ሀላፊ አቶ በቀለ ተመስገን÷ በአመቱ 1 ቢሊየን 361 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ከ1 ቢሊየን 746 ሚሊየን ብር በላይ በመሰብሰብ ከእቅድ በላይ ማሳካት መቻሉን ገልፀዋል።
ከተሰበሰበው ገቢም በቀጥታ ታክስ ከ1 ቢሊየን ብር በላይ ፣ ቀጥታ ካልሆነ ታክስ 495 ሚሊየን ብር፣ ታክስ ነክ ካልሆነ ገቢ 90 ሚሊየን ብር እንዲሁም ከማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ ከ155 ሚሊየን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል።
የተሰበሰበው ገቢም አጠቃላይ ከታቀደው እቅድ አንፃር 128 በመቶ መሆኑን ጠቁመው ገቢው ከ2014 በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀርም የ54 በመቶ ብልጫ እንዳለው ጠቁመዋል።
በ2016 በጀት አመትም ከግብር ከፋዩና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት የተሻለ ገቢ ለመሰብሰብ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑነወ ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።