አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የቤንች ሸኮ ዞን ለሶማሌ ክልል ከ20ሺ በላይ የተለያዩ ዝርያ ያላቸውን የደን ችግኞች በስጦታ አበረከተ፡፡
በዞኑ በሐምሌ 10 በአንድ ጀንበር 10 ሚሊየን ችግኝ በ164 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ላይ እንደሚተከልም ተጠቁሟል።
በዞኑ ግብርና መምሪያ የተፈጥሮ ደን እና አከባቢ ጥበቃ ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ጎጁ ኮይሳ÷ በዞኑ እስካሁን በተከናወኑ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች 6 ሚሊየን በላይ ጉድጓዶች መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል፡፡
ከመደበኛ የደን ችግኝ ባለፈም ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው የፍራፍሬ ችግኞች በዞኑ እንደሚተከልም ተናግረዋል።
ዞኑ ከ20 ሺ በላይ የተለያዩ ዝርያ ያላቸውን የደን ችግኞች ለሱማሌ ክልል በስጦታ አብርክቷል ሲሉ መናገራቸውን የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ዘግቧል፡፡