ቴክ

ፈጣኑ ተንሳፋፊ ባቡር

By ዮሐንስ ደርበው

July 14, 2023

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 7 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ጃፓናውያን ‘ፈጣኑን ተንሳፋፊ’ ባቡር እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

ከአራት ዓመታት በኋላ ሀዲድ ነክሶ መንገደኞችን ይዞ መክነፍ ይጀምራል የተባለው ይኼው ባቡር ‘ያማናሺ ማግሌቭ’ የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል።

ይህ ባቡር በሰባት ሰከንድ አንድ ኪሎ ሜትር እንደሚከንፍ የጃፓን ኢንፎርመር ዘገባ ያመላክታል።

ይህም ማለት 100 ኪሎ ሜትር ለመጓዝ 11 ደቂቃ ከ40 ሰከንድ ብቻ ይፈጅበታል ነው የተባለው።

ይኸው ‘ተወንጫፊ’ ባቡር ከአራት ዓመት በኋላ በፈረንጆቹ 2027 መንገደኞችን ይዞ መክነፍ ይጀምራል።

ቀደም ሲል ጃፓን ሬይል-ፓስ እንደዘገበው ደግሞ ባቡሩ ሌላ አስገራሚ ቴክኖሎጂ የተገጠመለት ነው።

ባቡሩ መንቀሳቀስ የሚጀምረው በዝግታ ሲሆን ፍጥነቱ እየጨመረ እየጨመረ ይሄዳል።

እንደ ዘገባው ባቡሩ ልክ በሰዓት 150 ኪሎ ሜትር መወንጨፍ ሲጀምር ጎማዎቹ ከሀዲዱ ይላቀቁና መንሳፈፍ ይጀምራል፤ ይህ ደግሞ የዚህ ባቡር ብቸኛ ስሪት ነው።

በዚህ ወቅት በሀዲዱ እና በባቡሩ ጎማዎች መካከል የነፋስ ማሳለፊያ ስንጥቅ ያህል ክፍተት የሚፈጠር ሲሆን፥ ባቡሩ በማግኔቲክ ኃይል አማካኝነት ከመሬት በ100 ሚሊ ሜትር ከፍ ብሎ መክነፍ ይጀምራል ተብሏል።

ይህም በባቡሩ ጎማዎችና በሀዲዱ መሀል የነበረውን የፍትጊያ ሰበቃ በማስቀረት ፍጥነቱ ይበልጥ እንዲጨምር እንደሚያደርገው ነው የተነገረው።