የሀገር ውስጥ ዜና

በቻይና የኢትዮጵያ የቡና ገበያ እያደገ ነው ተባለ

By Alemayehu Geremew

July 12, 2023

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቻይና የኢትዮጵያን ቡና ለመግዛት ያለው ፍላጎት እያደገ መምጣቱ ተገለጸ፡፡

በቻይና የኢትዮጵያን ቡና ከሌሎቹ ሀገራት ይልቅ መርጠው የሚጠጡ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ሺንዋ ዘግቧል፡፡

በቻይና ከባለፉት አምስት እና አሥርት ዓመታት ወዲህ እያደገ የመጣው የኢትዮጵያን ቡና የመፈለግ አዝማሚያ የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎችን እንዳበረታታና የሀገሪቷንም የውጭ ምንዛሬ ገቢ እያሳደገ እንደሆነ ነው የተመለከተው፡፡

የዓለም አቀፉ የቡና ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክተው የቻይና ዓመታዊ የቡና ፍጆታ መጠን ባለፉት አሥርት ዓመታት በአማካይ ከ15 በመቶ በላይ ጨምሯል፡፡

በቻይና ወጣቱ የኅብረተሰብ ክፍል በሀገሪቷ በተለያዩ ሁኔታዎች እንደ ባሕል ከሚጠጣው ሻይ ምርጫውን ወደ ቡና እያዞረ መሆኑም ነው የተነገረው፡፡

ይህ አዝማሚያ የቻይናን ቡና አስመጪዎች ከኢትዮጵያ አቻ የንግድ አጋር እንዲፈልጉ ማድረጉም ተመላክቷል፡፡

ከሽንዋ ጋር ቆይታ የነበራቸው የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ÷ ባለፈው ዓመት የተካሄደው ሁለተኛው የቻይና-አፍሪካ የኢኮኖሚ እና የንግድ ኤክስፖ ደግሞ የኢትዮጵያን ቡና ይበልጥ በቻይና ገበያ ውስጥ ለማስተዋወቅና የኅብረተሰቡን የቡና ምርጫ ወደ ኢትዮጵያ ለመለወጥ ማስቻሉን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በ2019/2020 በጀት ዓመት ወደ ቻይና የላከችው ቡና 4 ሺህ 200 ቶን ሲሆን ፥ በ2020/21 ደግሞ 8 ሺህ 400 ቶን መላኳ ተመላክቷል፡፡

ባለፈው ዓመት እስከ ፈረንጆቹ ሐምሌ 7 ባለው ጊዜ ውስጥ ደግሞ 11 ሺህ 200 ቶን ቡና በቻይና ገበያ መሸጡ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለሥልጣን ኢትዮጵያ ከፈረንጆቹ ሠኔ 2022 እስከ ሚያዝያ 2023 ባለው ጊዜ ውስጥ ከቡና ወጭ ንግድ 1 ነጥብ 1 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ማግኘቱን አስታውቋል፡፡

በተጠቀሰው ጊዜ ቻይና የኢትዮጵያ ቡናን ወደ ሀገሯ በማስገባት ሰባተኛዋ ሀገር ሆናለች።

የቡና ምርት ውጤቶች 24 በመቶ የሚሆነውን የሀገር ውስጥ ገቢ እንደሚያመነጩም ተዘግቧል፡፡