የሀገር ውስጥ ዜና

የኦሮሚያ ክልል የ2016 በጀት ከ221 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ ሆኖ ፀደቀ

By Amele Demsew

July 11, 2023

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኦሮሚያ ክልል የ2016 ዓ.ም በጀት ከ221 ነጥብ 517 ቢሊየን ብር በላይ ሆኖ ፀደቀ፡፡

የጨፌ ኦሮሚያ በአዳማ ከተማ እያካሄደ በሚገኘው መደበኛ ጉባዔ ለ2016 በጀት አመት የቀረበውን 221 ቢሊየን 517 ሚሊየን 956 ሺህ 655 ብር በጀት በአብላጫ ድምፅ አፅድቋል፡፡

ከቀረበው በጀት ለወረዳ እና ለከተሞች ወጪ 137 ነጥብ 8 ቢሊየን፣ ለክልሉ ወጪ 83 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር፣ ለክልሉ ካፒታል ወጪ 54 ነጥብ 25 ቢሊየን ብር እንዲሁም ለመጠባበቂያ 600 ሚሊየን ብር በጀት እንደተያዘ ተጠቅሷል፡፡

ለ2016 የተያዘው በጀት ካለፈው በጀት አመት ጋር ሲነጻጸ የ62 ነጥብ 88 ቢሊየን ብር ብልጫ እንዳለው ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም ጨፌ ኦሮሚያ በጉባዔው ለ2015 በጀት አመት የቀረበውን ተጨማሪ 13 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር በጀት አፅድቋል፡፡

በሌላ በኩል ጨፌው የ53 ዳኞችን ሹመት አጽድቋል።

እንዲሁም ኮሚሽነር አራርሳ መርዳሳን የክልሉ አስተዳደርና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አድርጎ ሾሟል፡፡