የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል ላይ የምታካሂደውን ልማት ጀርመን ትደግፋለች – ጄኒፈር ሊ ሞርጋን

By Alemayehu Geremew

July 11, 2023

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ሥጋትን ለመቀልበስና አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት በታዳሽ ኃይል ላይ የምታካሂደውን ልማት ጀርመን ለመደገፍ ዝግጁ መሆኗ ተገለጸ፡፡

በጀርመን የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ ትግበራ ልዩ መልዕክተኛ ጄኒፈር ሊ ሞርጋን ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳመለከቱት፤ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመግታት እና ከአየር ብክለት ነፃ ምጣኔ ሐብት ለመገንባት የምታደርገውን ጥረት ጀርመን መደገፏን ትቀጥላለች፡፡

ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት የምትደግፈው ጀርመን በዘርፉ ድጋፏን በሶስት በመቶ እንደምታደሳድግም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሃብቷን በመጠበቅ ለመልማት የምታደርገውን ጥረት አገራቸውን እንደምትደግፍ ጄኒፈር ሊ ሞርጋን አረጋግጠዋል።

በግብርናው ዘርፍ ላይ እየተከናወኑ ያሉትን ሥራዎች ልምድ በማካፈል፣ በገንዘብ እንዲሁም ዘመናዊ የግብርና መሣሪያዎች በማቅረብ እንደሚደግፉም ነው የጠቆሙት፡፡

ኢትዮጵያ እና ጀርመን በኃይል ዘርፍ ያላቸው የትብብር ማዕቀፍ ዓለም ዓቀፋዊውን ከአየር ብክለት ነጻ የሆነ የኃይል አቅርቦት ሽግግሩን እንደሚያፋጥንም አንስተዋል፡፡

በዮናታን ዮሴፍ