የሀገር ውስጥ ዜና

ሩሲያ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመከላከል የምታደርገውን ጥረት እንደምትደግፍ ገለጸች

By Melaku Gedif

July 08, 2023

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመከላከል ለምታደርገው ጥረት ሩስያ ትብብርና ድጋፍ እንደምታደርግ በኢትዮጵያ የሩስያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተርኪን ተናገሩ።

የአየር ሁኔታ መለወጥ የውሃ ሃብትን በመቀነስ፣ በግብርና ምርት ላይ ጫና በማሳደርና ሌሎች ውስብስብ ችግሮች በመፍጠር ፈተና መሆኑን የጠቀሱት አምባሳደር ኢቭጌኒ ተርኪን ÷ ችግሩም ዓለም አቀፍ መሆኑን ገልጸዋል።

በአንድ አህጉር ወይንም ቀጣና የሚወሰን ባለመሆኑ ዓለም አቀፍ ትብብርን በማጠናከር ተጽእኖውን መከላከል ያስፈልጋል ብለዋል።

ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያን ጥረት አድንቀው÷ የአየር ንብረት ተጽእኖን ለመከላከል በምታደርገው ጥረት የሩስያ ትብብርና ድጋፍ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ ልማት የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እያከናወነች ያለውን ተግባር ሩሲያ በምርምር ዘርፍ መደገፍ ትሻለችም ነው ያሉት።

ለዚህም ሁለቱ ሀገራት ላለፉት 30 ዓመታት በባዮሎጂካል የምርምር ዘርፍ በትብብር ሲያከናውኗቸው የቆዩ ተግባራትን ለማጠናከር እየሰሩ እንደሆነ መጥቀሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በኢትዮጵያ በቋሚነት የሚሰራ የባዮሎጂካል የምርምር ኢንስቲትዩት ለማቋቋም እቅድ መኖሩንም ጠቁመዋል።