የሀገር ውስጥ ዜና

በትግራይ ክልል የግብር መክፈያ ጊዜ ለሶስት ወር ተራዘመ

By Amele Demsew

July 07, 2023

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የትግራይ ክልል ግዚያዊ መስተዳድር ካቢኔ ትናንት ባደረገው መደበኛ ስብሰባ በክልሉ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት የተለያዩ ውሳኔዎች አሳልፏል።

ከውሳኔዎቹ መካከል የ2015 በጀት ዓመት ግብር መክፈያ ጊዜ ማራዘም አንዱ ሲሆን በውሳኔው መሰረት በክልሉ ግብር የሚከፈልበት ጊዜ እስከ መስከረም 30 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ እንዲራዘም መወሰኑ ተገልጿል።

የንግድ ፈቃድ የሚታደስበት ወቅትም በተመሳሳይ እስከ መስከረም 30 2016 ዓ.ም ተራዝሟል።

በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በነበረው ጦርነት ምክንያት የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን ለመገንባት ውል ገብተው ግዴታቸውን ያልተወጡ ኮንትራክተሮች ውላቸው እንዲያሳድሱም ውሳኔ መሰጠቱን ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ ርእሰ መስተዳድር ፅሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።