አዲስ አበባ፣ ሰኔ 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በፖርቹጋል የሚገኘው ‘ቦቢ’ የተባለው የ31 ዓመቱ ውሻ በእድሜ ትልቁ ውሻ በመሆን በዓለም ድንቃድንቅ መዝገብ ላይ ስሙ ሰፍሯል።
ውሻው በፖርቹጋል ‘ራፌይሮ ዶ አሌንቲዮ’ የሚል ስያሜ ከተሰጣቸው የውሻ ዝርያዎች የተገኘ ሲሆን እነዚህ ውሻዎች አማካይ እድሜያቸው ከ12 እስከ 14 ዓመት ነው ተብሏል፡፡
ይሁን እንጂ ‘ቦቢ’ የተባለው ይህ ውሻ ከተቀመጠው አማካይ እድሜ በላይ 31 ዓመታትን በህይወት በመኖር የምድራችን የምንጊዜም ‘አዛውንቱ ውሻ’ የሚለውን ስያሜ አግኝቷል።
ቦቢ በፈረንጆቹ ሰኔ 11 ቀን 1992 የተወለደ ሲሆን በትናንትናው እለት በእድሜ ትልቁ ውሻ በመባል የዓለም ድንቃድንቅ መዝገብ ላይ ስሙ ሰፍሯል፡፡
የውሻው ባለቤት ሊዮኔል ኮስታ እንደተናገሩት÷ ቦቢ ረጅም አመታትን በጤና እንዲኖር ያስቻለው ሚስጥር ከከተማ ርቆ በተረጋጋ እና እና ሰለማዊ በሆነ ስፍራ መኖር መቻሉ ነው፡፡
ቦቢ ቤት ውስጥ ታስሮ የማያውቅና በአካባቢው ባሉ ደኖች እና እርሻ ቦታዎች በነፃነት ሲንቀሳቀስ ኖሯል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
እንደ ዓለም ድንቃድንቅ መዝገብ ቀደም ሲል በአውስትራሊያ የሚገኘው እና ካትል ዶግ የተባለ ዝርያ ያለው ውሻ 29 ዓመት ከ5 ወር በመቆየት በእድሜ ትልቁ ውሻ ክብረ ወሰንን ይዞ መቆቱን አናዶሉ በዘገባው አስታውሷል፡፡