የሀገር ውስጥ ዜና

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ የኢትዮጵያ እና ጅቡቲ ግንኙነት ልዩ ትርጉም እንዳለው ገለጹ

By Shambel Mihret

July 06, 2023

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የኢትዮጵያ እና የጅቡቲ ግንኙነት ጥብቅና ልዩ ትርጉም አለው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ  ከጅቡቲ የሕዝብ ለሕዝብና የዲፕሎማሲ ልዑክ  ጋር ከተወያዩ በኋላ ባደረጉላቸው የእራት ግብዣ ላይ እንደተናገሩት÷ዘመናዊ የሕዝብ ለሕዝብ ዲፕሎማሲ ባልነበረበት ጊዜ ሳይቀር የሀገራቱ ሕዝቦች ትስስር ጠንካራ ነበር፡፡

ፕሬዚዳንቷ አሁን ላይ  የኢትዮጵያ እና ጅቡቲ የሁለትዮሽ  ግንኙነት ጥብቅ እና  ልዩ ትርጉም አለው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

በመድረኩ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በበኩላቸው÷  የጅቡቲ ልዑካን ቡድን አባላት  የኢትዮጵያ ጉብኝት መጠነ ሰፊና የሀገራቱን ስትራቴጂካዊ ግንኙነቱን ይበልጥ ያጠናክራል ብለዋል።

የጅቡቲ የሕዝብ ለሕዝብ እና የዲፕሎማሲ ልዑክ  መሪና የሀገር ውስጥ ሚኒስትር ዴዔታ ሲራጅ ኦማር÷ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስሩ በንግዱ ዘርፍ  እንዲጠናከር ሁኔታዎችን ማመቻቸት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

የጅቡቲ የሕዝብ ለሕዝብ እና የዲፕሎማሲ ልዑክ  በኢትዮጵያ ቆይታው በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርና በውይይት መድረኮች ሲሳተፈ መቆየቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡