Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በየዓመቱ ለሳተላይት መረጃ ይወጣ የነበረውን 2 ነጥብ 8 ሚሊየን ዶላር ማስቀረት መቻሉ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ የመሬት ምልከታ ሳተላይት አገልግሎት ላይ በመዋሉ በየዓመቱ ለሳተላይት መረጃ ይወጣ የነበረውን 2 ነጥብ 8 ሚሊየን ዶላር ማስቀረት መቻሉን የስፔስ ሳይንስና ጂኦ-ስፓሻል ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ኢንስቲትዩቱ የምህንድስና ዲዛይን የሚሰራበትን ሂደት የሚያሳይ መጽሐፍና የሳተላይት መተግበሪያ ይፋ አድርጓል።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አብዲሳ ይልማ የኢትዮጵያን የቆዳ ስፋት የሚሸፍን 2 ሜትር የሳተላይት ጥራት (ሪዞሉሽን) ያለው መረጃ እንደ አገር እየተገኘ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህም ኢትዮጵያ በዓመቱ ለሳተላይት መረጃ የምታወጣውን 2 ነጥብ 8 ሚሊየን ዶላር አስቀርቷል ብለዋል።

የሳተላይት መረጃ ለተፈጥሮ ኃብት አስተዳደርና የተራቆቱ አካባቢዎችን መልሶ ለማልማት የላቀ ጠቀሜታ ያለው መሆኑንም አስረድተዋል።

የሳተላይት መረጃዎች የተፈጥሮ አደጋን ቀድሞ ለመከላከልና ወቅታዊ መረጃዎችን በማግኘት ለአገር ልማትና እድገት ያለውን አስተዋጽዖም ጠቅሰዋል።

የምህንድስና ዲዛይን የሚሰራበትን ሂደት ለማሳየት ይጠቅማል በሚል የተዘጋጀው መጽሐፍ ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮና የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ በማገናዘብ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።

መጽሐፉ የምህንድስና ዲዛይንን ይዘትና ውጤቱን የሚያስረዳ መሆኑን ጠቅሰው፤ የሲስተም ኢንጂነሪንግ ትግበራን እውን ለማድረግና ለችግሮች መፍትሔ ለመስጠት ያግዛል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በታኅሳስ 2012 ዓ.ም ኢትዮጵያ በታሪኳ የመጀመሪያውን “ኢቲ አር ኤስ ኤስ-01” የመሬት ምልከታ ሳተላይት ከቻይና የሳተላይት ማስወንጨፊያ ጣቢያ ወደ ሕዋ መላኳ ይታወሳል።

በታኅሳስ 2013 ዓ.ም ደግሞ “ኢቲ-ስማርት-አር ኤስ ኤስ” የተሰኘችውን ሁለተኛዋን የመሬት ምልከታ ሳተላይት በተመሳሳይ አምጥቃለች።

Exit mobile version