የሀገር ውስጥ ዜና

ከ4 ነጥብ 6 ሚሊየን ተፈናቃዮች 3 ነጥብ 5 ሚሊየኑ ተመልሰው ተቋቁመዋል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

By ዮሐንስ ደርበው

July 06, 2023

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በ10 ክልሎች ከነበሩት 4 ነጥብ 6 ሚሊየን ተፈናቃዮች መካከል 3 ነጥብ 5 ሚሊየን ወገኖች ተመልሰው መቋቋማቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በምላሻቸውም ጉዳት የደረሰባቸውን ክልሎች መልሶ ለማቋቋም በመንግሥት፣ በዳያስፖራው፣ በረድኤት ድጅቶች እና በባለሃብቶች በኩል የተቀናጀ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አስገንዝበው፤ ይሄው ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

ዜጎችን እያፈናቀሉ ቦታን ማስፋት ስለማይቻል÷ አሁንም ተፈናቅለው ያሉ ወገኖችን የመመለሱ ተግባር እንደሚጠናከር አስረድተዋል፡፡

የሚመለከታቸው አካላትም ሃላፊነታቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል፡፡

ለተፈናቃዮች ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ካለፈው ጥቅምት ወር ወዲህ ብቻ ለአማራ፣ አፋር እና ትግራይ ክልሎች 370 ሺህ ቶን የምግብ ርዳታ መላኩንም ጠቁመዋል።

በዮሐንስ ደርበው