አዲስ አበባ፣ ሰኔ 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የተቋማት ብሎም በግለሰብ ደረጃ የተለያየ ግልጋሎት የሚሰጡ ድረ‐ገጾች ለመረጃ መዝባሪዎች የጥቃት ኢላማ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
ይህን ተጋላጭነት ለመቀነስ ከሚያስችሉ የመከላከያ መንገዶች መካከል ሶፍትዌሮችን ማዘመን (አፕዴት ማድረግ)፣ የዶሜይን ደህንነትን ማስጠበቅ፣ ለተጠቃሚዎች የተሰጡ አላስፈላጊ አካውንቶችንና ፍቃዶችን ማጥፋት፣ ወሳኝና ከፍተኛ ክፍተቶችን መሙላት ወይም መጠገን ፣ ግልጋሎት የማይሰጡ ኦፕሬቲንግ ሲስተሞችን፣ መተግበሪያዎችን እና መገልገያዎችን በአዲስ መተካት ይጠቀሳል፡፡
እንዲሁም በዝውውር ላይ የሚገኝን የመረጃ ደህንነት ማስጠበቅ በዚህም የድረ-ገፅ ተገልጋዮች ግላዊነታቸው እንዲጠበቅ ምስጠራን መጠቀም ድረ-ገጽዎን ከጥቃት ለመከላከል ከሚያስችሉ መንገዶች ይጠቀሳሉ፡፡
በተጨማሪም ቅጂ ወይም ቀሪ መያዝ ለምሳሌም ወሳኝ መረጃዎችንና የስርዓት ማስተካከያዎችን ሁልጊዜም አውቶማቲክ ቅጂ መያዣን መጠቀም፣ የቀሪ መያዣ ሚድያዎን ደህንነቱ በተጠበቀ እና የመይገባው አካል እጅ እንዳይገባ አርቆ ማስቀመጥ ይገባል።
የዌብ መተግበሪያዎችን እና የዌብ ሰርቨሮችን ደህንነት ማስጠበቅ እንዲሁም ታማኝና ደህንነቱ የተጠበቀ (ቢቻል ቀጣይነት ያለው ቴክኒካል ድጋፍ እንደ ፋየርዎል፣ SSL ሰርቲፊኬቶች፣ የርቀት ቅጂ ማስቀመጫ፣ ኔትዎርክ ቁጥጥር ወዘተ. የሚሰጥ) የድረ-ገፅ አስተናጋጅ መጠቀምም ድረ-ገፆዎን ከጥቃት ለመከላከል ከሚያስችሉ መንገዶች መካከል ተጠቃሽ ነው፡፡