የሀገር ውስጥ ዜና

ከ153 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተገነባው የፌዴራል ፖሊስ የምዕራብ ፈጥኖ ደራሽ ካምፕ ተመረቀ

By ዮሐንስ ደርበው

July 04, 2023

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሶሳ ከተማ ከ153 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባውን የፌዴራል ፖሊስ የምዕራብ ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ ካምፕ ተመረቀ፡፡

በ2007 ዓ.ም ግንባታው የተጀመረው ካምፑ÷ የመኝታ፣ የእንግዳ ማረፊያ፣ ክሊኒክ እና የተለያዩ የስፖርት ማዘውተሪያዎችን ያካተተ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን÷ ካምፑ በክልሉ ያለውን ሠላም ዘላቂ ለማድረግ እየተደረገ ላለው ጥረት ትልቅ ፋይዳ አለው ብለዋል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል የወቅቱ የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ሕብረት ድርጅት ፕሬዚዳንት÷ ሠላም የማስከበር ሥራዎችን ለማጠናከር በክልሎች መሠል ካምፖችን ወደሥራ እያስገቡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ቀጠናውን ከየትኛውም የጸረ-ሠላም እንቅስቃሴ ነጻ በማድረግ ሠላሙን ለማረጋገጥ የፌዴራል ፖሊስ ተልዕኮውን ይወጣል ማለታቸውን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ እና የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በካምፑ ግቢ አረንጓዴ ዐሻራቸውን አኑረዋል፡፡