ቢዝነስ

የተለያዩ ክልሎች ለባለሐብቶች አዋጭ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ማዘጋጀታቸውን አስታወቁ

By Alemayehu Geremew

July 03, 2023

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) መስፈርቱን ለሚያሟሉ ባለሐብቶች ምቹ እና አዋጭ የኢንቨስትመንት አማራጮች ማዘጋጀታቸውን የተለያዩ ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች አስታወቁ፡፡

የኦሮሚያ እና ሲዳማ ክልሎች እንዲሁም የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ባለሐብቶች መዋዕለ-ንዋያቸውን በክልሎቹ እና በከተማ አስተዳደሩ እንዲያፈሱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ኢንቨስትመንት እና ኢንዱስትሪ ቢሮ የፖቴንሺያል እና ፕሮሞሽን ዳሬክተር ስዩም ሞሲሳ ÷ ክልሉ በእርሻ እና እንስሳት ልማት ዘርፍ ዕምቅ ሐብት ቢኖረውም እምብዛም አልተሰራበትም ብለዋል፡፡

እስካሁን 90 በመቶው የኢንቨስትመንት አማራጭ በሀገር ውስጥ ባለሐብቶች ብቻ እንደሚያዝ አመላክተዋል፡፡

የውጭ ባለሐብቶችን ለመሳብ የቴክኖሎጂ እና ዘመናዊ አሰራሮችን ተግባራዊ እያደረጉ ስለመሆኑም ጠቁመዋል፡፡

የሲዳማ ክልል የኢንቨስትመንት ኮሚሽን የፕሮሞሽን ፣ መረጃ እና ፍቃድ ዳሬክተር ታሪኩ ሮባ በበኩላቸው ÷ በክልላቸው ለግብርና እና ግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ምቹ የተፈጥሮ ሐብት መኖሩን አንስተዋል፡፡

የድሬ ዳዋ ከተማ አስተዳዳር የኢንቨስትመንት ጥናት እና ፕሮሞሽን ቡድን መሪ አበራ መንግስቴ÷ ባለሐብቱ በማኑፋክቸሪንግ እና አገልግሎት ዘርፍ ላይ እንዲሰማራም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

መሥፈርቱን ለሚያሟሉ ባለሐብቶች 31 ፕሮጀክቶችን ለይተው ማዘጋጀታቸውንም አመላክተዋል፡፡

መሬት ወስደው ወደ ሥራ ባልገቡ አልሚዎች ላይ እርምጃ በመውሰድ ማልማት ለሚችሉ እያስተላለፉ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡

በማርታ ጌታቸው