የሀገር ውስጥ ዜና

ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ በጌዲኦ ዞን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብርን አስጀመሩ

By Melaku Gedif

July 03, 2023

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በደቡብ ክልል ጌዲኦ ዞን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብርን አስጀምረዋል፡፡

በመርሐ-ግብሩ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸውን ጨምሮ የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ አመራሮች መገኘታቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ÷ የጌዴኦ ሕዝብ አካባቢውን በመንከባከብ አረንጓዴ የሆነ አካባቢን ለመፍጠር የሚያደርገው ጥረት አድንቀዋል፡፡

ሠላማቸውን የመጠበቅ ባሕላቸውን ለሌላው እንዲያጋሩም በአጽንኦት አሳስበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ዘላቂ ሠላምን ለማስፈን የዕለት ከዕለት ጥረት በተገቢው መንገድ ካልተደረገ ዕውን ማድረግ አስቸጋሪ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በመሆኑም እንደ አረንጓዴ ዐሻራ ካሉ የልማት ሥራዎች ጎን ለጎን የጋራ ሠላምን ለማጎልበት የበለጠ ተባብሮ መስራት አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡