አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 22፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ከተገኘባቸው ሰዎች ውስጥ አብዛኞቹ በለይቶ ማቆያ ውስጥ የነበሩ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ገለፀ።
ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በኢትዮጵያ በአጠቃላይ በኮሮና ቫይረስ የተገኘባቸው 131 ሰዎች መሆናቸውን የጠቀሰው ኢኒስቲትዩቱ፥ ከእነዚህም 69 ሰዎች ማለትም 53 በመቶ በአስገዳጅ የለይቶ ማቆያ ከነበሩ መንገደኞች ውስጥ መሆኑ ተረጋግጧል ብሏል።
የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አስቻለው አባይነህ እንደገለጹት ፥የአለም ጤና ድርጅት የኮሮና ቫይረስ በሽታን ለመከላከል ሀገሮች ማድረግ ስለሚኖርባቸው ጥንቃቄዎች መልክቶችን እያስተላለፈ ይገኛል።
ከዚህም ውስጥ ለበሽታው የተጋለጡ ሰዎች በለይቶ ማቆያ ውስጥ ማስቀመጥ አንዱ ሲሆን፥ በኢትዮጵያም ማንኛውም ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባ መንገደኛ ለ14 ቀናት በለይቶ ማቆያ እንዲገባ ተወስኖ ከውጭ ሀገር ተመላሾች ወደ ህብረተሰቡ ሳይቀላቀሉ በተዘጋጀው የለይቶ ማቆያ ቦታዎች እንዲቆዩ እየተደረገ ይገኛል።
ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በአዲስ አበባ እንዲሁም በክልል ከሚገኙ የለይቶ ማቆያ ቦታዎች በተገኘው መረጃ መሰረት ከ16 ሺህ በላይ ከውጭ ሀገር ተመላሾች ወደ ለይቶ ማቆያ የገቡ ሲሆን፥ የ14 ቀን ቆይታ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁ እና የላብራቶሪ ምርመራ ተደርጎላቸው ከኮሮና ቫይረስ ነጻ የሆኑ 5 ሺህ 342 ሰዎች ወደ ህብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ መደረጉንም አስታውቋል።
በዚህም በቫይረሱ የተያዙ በርካታ ሰዎችን ማግኘት የተቻለ ሲሆን፥ ይህም የቫይረሱን
ስርጭት ለመከላከል በከፍተኛ ሁኔታ አግዟል ብለዋል።
አቶ አስቻለው አባይነህ አክለውም መንገደኞች በለይቶ ማቆያ እንዲቆዩ መደረጉ የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር የተወሰደ እርምጃ መሆኑን በመረዳት በማቆያ ውስጥ በሚሆኑበትም ወቅት ከሌሎች ጋር ባለመገናኘት ራሳቸውን ሊጠብንቁ ይገባል ብለዋል።
ወደ ቤተሰቦቻቸው ሲቀላቀሉም ለህብረተሰቡ የሚተላለፉ መልዕክቶችን ተግባራዊ እንዲያደርጉ መልዕክት እንዲያስተላልፉ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢኒስቲትዩቱ ያወጣው መረጃ ያመለክታል።
በተጨማሪም ህብረተሰቡ ለተለያዩ ጉዳዮች በአንድ ቦታ መሰባሰብን በማስወገድ፣ እጅን አዘውትሮ በመታጠብ፣ በአካል ንክኪ የሚደረግ ሰላምታን በመተውና አካላዊ መራራቅን ተግባራዊ በማድረግ የበሽታውን ስርጭት እንዲከላከል በአሳስበዋል።
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።