አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከቻይናው ዙምላይን የእርሻ መሣርያ አምራች ኩባንያ ጋር የንግድ ስምምነት ተፈራርሟል።
የስምምነቱ ሰነድ ሁለት ምዕራፎችን ያካተተ ሲሆን÷የመጀመሪያው በከፊል የተገጣጠሙ የእርሻ መሣሪያዎችን በማስመጣትና ቀሪ የገጠማ ሥራዎችን በሀገር ውስጥ በማጠናቀቅ ለገበያ ማቅረብን ያካትታል ተብሏል።
በሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ የእርሻ መሣሪያዎችን አስመጥቶ በኮርፖሬሽኑ ማዕከል ሙሉ በሙሉ በመገጣጠም ለገበያ ለማቅረብ ስምምነት ላይ መደረሱ ተገልጿል፡፡
ስምምነቱ የበቆሎ፣ የሩዝ እና የአኩሪ አተር ምርቶችን ለመሰብሰብ የሚያገለግሉ የእርሻ መሣሪያዎችን እንደሚያካትት የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡
ለንግድ ትስስር ወደ ቻይና ያቀናውን ልዑክ የመሩት የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) የዙምላይን ቻንግ ሺ ኢንደስትሪያል ፓርክን ጎብኝተዋል፡፡
በዚህም በፓርኩ ያለውን የቴክኖሎጂ እድገትና የፈጠራ ሥራ ያደቁ ሲሆን÷ በርካታ ቴክኖሎጂዎችን ከኢትዮጵያ ሁኔታ ጋር ማላመድ እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡