የሀገር ውስጥ ዜና

ለውጪ ገበያ ከቀረበ የእንስሳት ተዋፅኦ ከ80 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ

By Melaku Gedif

July 01, 2023

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት 11 ወራት እሴት ተጨምሮበት ለውጪ ገበያ ከቀረበ የእንስሳት ተዋፅኦ ከ80 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የእንስሳት ልማት ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሳህሉ ሙሉ (ዶ/ር) እንዳሉት÷ ባለፉት 11 ወራት የሥጋ ፣ የማር ፣ የግመል ወተትና የእርድ ተረፈ- ምርቶችን ለተለያዩ ዓለም ሀገራት ለመላክ ተችሏል።

በዚሁ ወቅት 20 ሺህ ቶን መጠን ያለው የእንስሳት ተዋፅኦዎችን ለውጭ ገበያ የቀረቡ ሲሆን÷ ኢንስቲትዩቱ የዕቅዱን 90 በመቶ ለማሳካት መቻሉን አስረድተዋል።

ኢንስቲትዩቱ በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ ከእንስሳትና የእንስሳት ተዋፅኦ 137 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ለማግኘት አቅዶ እየሰራ ሲሆን÷ ባለፉት 11 ወራት 86 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ መገኘቱን ጠቁመዋል።

በበጀት ዓመቱ የእንስሳት ተዋፅኦዎች እሴት ተጨምሮባቸው ለውጪ ገበያ እንዲቀርቡ በማድረጉ በኩል ከአምናው ጋር ሲነጻጻር የተሻለ ውጤት መመዝገቡን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በብዛት ለውጪ ገበያ የምታቀርበው የበግና የፍየል ምርቶች መሆናቸውን አብራርተዋል።

የተለያዩ የዓለም ሀገራት ከኢትዮጵያ የዳልጋ ከብት ሥጋን ለመግዛት ፍላጎት ቢኖራቸውም ምርቱ በሀገር ውስጥ ያለው ዋጋ ከፍተኛ መሆኑ በሚፈለገው ልክ ለውጪ ገበያ እየቀረበ አይደለም ነው ያሉት።

ለውጭ ገበያ ከሚቀርቡ የተረፈ-ምርት ውጤቶች መካከል የእንስሳት ሆድ ዕቃ፣ ቀንድ እና ቆዳ ተጠቃሽ እንደሆኑ መግለጻቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡