አዲስ አበባ፣ ሰኔ 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የስሜት መቃወስ በመንፈስ ጭንቀት ምክንያት የሚከሰት የአዕምሮ ህመም መሆኑን የዘርፉ ምሁራን ያስረዳሉ፡፡
የስሜት መቃወስ በታማሚው ላይ የስሜት መለዋወጥን የሚያስከትል ሲሆን÷ታማሚው አንዳንዴ በጭንቀት፣ ድባቴ ውስጥ ሲሆን ደስታ እና የእንቅስቃሴ ፍላጎት ማጣት እንዲሁም የተስፋ ማጣት ስሜት ውስጥ ይገባል፡፡
በሌላ ጊዜ ደግሞ የታማሚው ስሜት በመቀየር ከፍተኛ የደስታ ስሜት፣ ሳቅ፣ ጥንካሬ እንዲሁም ያልተለመደ ንዴትን ሊያሳይ እንደሚችል ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡
የተጋነነ በራስ መተማመን፣ ከልክ ያለፈ የእንቅስቃሴ ፍጥነት፣ያልተለመደ ንግግር፣ ትንኮሳ፣ የእንቅልፍ ማጣት ወይም ብዙ ሰዓት መተኛትም የህመሙ ምልክቶች መሆናቸውን ማዮ ክሊኒክ መጽሔት ዘግቧል፡፡
እነዚህ የስሜት መቃወስ ምልክቶችም ታማሚውን ለእንቅልፍ ችግር፣ አቅም ማነስ፣ የእንቅስቃሴ ፍላጎት አለመኖር፣ የመወሰን ችግር እና የማሰብ ችሎታውን በከፍተኛ ደረጃ ሊጎዱት ይችላሉ፡፡
የህመሙ ምክንያቶች በግልፅ ባይታወቁም በሰዎች ዘንድ የሆርሞን መቀያየር የሚፈጥረው የአዕምሮ ውቅር ለውጥ፣ የስነ ልቦና ቀውሶች እንዲሁም በዘር ከወላጅ ወደ ልጅ ሊተላለፍ እንደሚችል በዘገባው ተመላክቷል፡፡
ይህ የስሜት መቃወስ በሰዎች ላይ በተለያዩ ጊዜያት የሚከሰት ሲሆን÷አንዳንድ ሰዎች ህመሙን ሲረዱት እና ምልክቱን ሲያሳዩ ሌሎች ሰዎች ግን የህመሙን ስሜት እንደማይገነዘቡት ተጠቅሷል፡፡
ስለሆነም የስሜት መቃወስ በራሱ የሚድን ባለመሆኑ ከላይ የተጠቀሱት ስሜቶች በሚስተዋሉበት ጊዜ ብዙ ሳይቆዩ የስነ ልቦና ባለሙያዎችን ማማከር እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡