አዲስ አበባ፣ ሰኔ 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ቤቶችን መሰረተ ልማት ለማሻሻል የትምህርት ባለድርሻዎችንና ህብረተሰቡን ያሳተፈ ሀገር አቀፍ የሕዝብ ንቅናቄ ሊያካሄድ መሆኑን አስታውቋል።
ሀገር አቀፍ ንቅናቄው ሰኔ 25 ቀን 2015ዓ.ም የመንግስት ከፍተኛ አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በይፋ እንደሚጀመር ተገልጿል።
የትምህርት ሚኒስትር ብርሀኑ ነጋ (ፕ/ር)÷ ሀገር አቀፍ ንቅናቄው ህብረተሰቡ የትምህርት መሠረተ-ልማት በማሻሻል የመማር ማስተማሩን ሂደት በባለቤትነት እንዲደግፍ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ገልፀዋል።
የትምህርት ቤቶችን መሰረተ ልማት የማሻሻል ስራ ለመንግስት ብቻ የተተወ ኃላፊነት አለመሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሩ÷በየደረጃው ያለው ማህበረሰብና ልዩ ልዩ አካላት ተሳትፏቸውን ሊያሳድጉ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
አብዛኞቹ የመጀመሪያ፣ መካከለኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ንጹህና በቂ ውሃ እንደማያገኙ፣ የኤሌክትሪክ ፣ የመፀዳጃ ፣ የመማሪያ ፣የቤተ መጻሕፍት ፣ የቤተ ሙከራ ፣ የስፖርት ማዘውተሪያና ሌሎችም ችግሮች እንዳሉባቸው ነው የገለጹት፡፡
በሀገሪቱ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚስተዋሉ ዋነኛ የትምህርት መሰረተ ልማት ችግሮችን ለመፍታት እየተሰራ እንደሆነ መግለጻቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡
በዚህም ባለሃብቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ አርቲስቶች፣ ዳያስፖራ አባላት፣ ልዩ ልዩ አደረጃጀቶች፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ማህበራትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በንቅናቄው የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡