የሀገር ውስጥ ዜና

ቦርዱ የወላይታ ዞን የድጋሚ ሕዝበ ውሣኔ በዞን ደረጃ ጊዜያዊ ውጤት ይፋ አደረገ

By Feven Bishaw

June 24, 2023

 

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የወላይታ ዞን የድጋሚ ሕዝበ ውሣኔ በዞን ደረጃ የጊዜያዊ ውጤት ይፋ አድርጓል፡፡

ቦርዱ ሰኔ 12 ቀን 2015 ዓ.ም. በ1 ሺህ 812 ምርጫ ጣቢያዎች ላይ ያስፈጸመውንና 849 ሺህ 896 መራጮች ድምፅ የሰጡበትን የወላይታ ዞን የድጋሚ ሕዝበ ውሣኔ የውጤት ማዳመሩን ሥራ በዞኑ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሲያከናወን መቆየቱ ይታወቃል።

በዛሬው ዕለትም ቦርዱ የውጤት የማመሳከሩንና የማዳመሩን ሥራ በማጠናቀቅ በዞን ደረጃ የጊዜያዊ ውጤቱን ይፋ ማድረጉን ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በዚህም 760 ሺህ 285 ድምፅ ሰጪዎች የስድስቱ ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎች በአንድ የጋራ ክልል መደራጀትን ደግፈው ድምፅ ሰጥተዋል።

42 ሺህ 413 ድምፅ ሰጪዎች ደግሞ ሳይደግፉ ድምፅ ሰጥተዋል።