Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በአማራ ክልል ያለው የኢንቨስትመንት ፍሰት እየጨመረ መምጣቱ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ያለው የኢንቨስትመንት ፍሰት እየጨመረ መምጣቱን የክልሉ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታውቋል፡፡

የቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ይኸነው አለም ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ በአማራ ክልል ባለፉት 11 ወራት ውስጥ 4 ሺህ 146 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደዋል፡፡

ፈቃድ የወሰዱት ባለሃብቶች 415 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ካፒታል እንዳስመዘገቡ የጠቆሙት ሃላፊው÷ ለ916 ሺህ 971 ዜጎች የስራ ዕድል እንደሚፈጥሩም ተናግረዋል፡፡

በክልሉ አመራር፣  የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች እና ዳያስፖራው ዘንድ የተፈጠረው መነሳሳት እንዲሁም በክልሉ አንጻራዊ ሰላም በመኖሩ  የኢንቨስትመንት ፍሰቱ እየጨመረ መምጣቱን አንስተዋል፡፡

በክልሉ ባለፉት ሶስት ዓመታት ለ8 ሺህ 469 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ እንደተሰጠም አቶ ይኸነው አስታውሰዋል፡፡

የክልሉን ፀጋ መሰረት በማድረግ በ6 የኢንቨስትንት ቀጠናዎችና ዋና ዋና ኢንቨስትመንት አማራጮች እንደተለዩ ጠቅሰው÷አሰራር የሚያጓትቱ መመሪያዎች ላይ ማሻሻያ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

በዚህም የጣና ዙሪያና የቡሬ  ኢንዱስትሪ ልማት ቀጠና፣  የምስራቅ አማራና የአባይ ሸለቆ ኢንዱስትሪ ልማት ቀጠና፣ የሰሜን ምዕራብ ኢንዱስትሪ ልማት ቀጠና እንዲሁም የተከዜ ተፋሰስ (የዋግ  ኢንቨስትመንት) ቀጠና ዋና ዋናዎቹ  መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

የፈቃድ አገልግሎት አሰጣጥን ድጂታላይዝ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው ÷በክልሉ መዋዕለ ንዋይ ለማፍሰስ  የሚመጡ ባለሃብቶች ፍሰት እየጨመረ  መምጣቱንም አመላክተዋል፡፡

 

በየሻምበል ምህረት

 

Exit mobile version