የሀገር ውስጥ ዜና

አበረታች ቅመሞችን በመጠቀም የተጠረጠሩ 7 አትሌቶች ጉዳያቸው እየተጣራ መሆኑ ተገለጸ

By Alemayehu Geremew

June 21, 2023

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 14፣ 2015(ኤፍ ቢ ሲ) አበረታች ቅመሞችን በመጠቀም የተጠረጠሩ ሰባት አትሌቶች ጉዳያቸው እየተጣራ መሆኑን የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን አስታወቀ።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር መኮንን ይደርሳል አበረታች ቅመሞች መጠቀም አስመልክቶ በተደረገ ምርመራ ሰባት አትሌቶች የመጀመሪያ ደረጃ ተጠርጣሪ ሆነዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በዚህም አራት አትሌቶች በኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን ጉዳያቸው መያዙን አስረድተዋል፡፡

የሶስቱ አትሌቶች ደግሞ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ምርመራና ቁጥጥር ስራን በዋናነት በሚያከናውነው ‘ወርልድ አትሌቲክስ ኢንቲግሪቲ ዩኒት’ በተባለው አካል ጉዳያቸው እየታየ መሆኑን ገልጸዋል።

በአትሌቶቹ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ የመስጠት ሂደቱ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው÷ በቀጣይ የሚተላለፉ ውሳኔዎች ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረጉ አረጋግጠዋል፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት አበረታች ቅመሞች በመጠቀም የሚያዙ አትሌቶች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል ያሉት አቶ መኮንን የተከለከሉ ንጥረ ነገሮችን የሚጠቀሙ አትሌቶች ላይ ቅጣት ከማስተላለፍ ባሻገር ለዚህ አይነት ተግባር ሊገፋፏቸው የሚችሉ በዙሪያቸው በሚገኙ ባለሙያዎች ላይም ምርመራ እየተደረገ ነው ብለዋል።

አትሌት አሰልጣኞች፣ ወኪሎች፣ የጤና ባለሙያዎችና ተቋማት ላይ ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሚገኝም ነው ዋና ዳይሬክተሩ የተናገሩት።

እስካሁን አንድ የመድኃኒት ቤት ላይ የሶስት ወር እገዳ መጣሉን እና አንድ የጤና ባለሙያ በሕግ ቁጥጥር ስር ውሎ የፍርድ ሂደቱን በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኝ ለአብነት አንስተዋል።

የናሙና ምርመራዎችን በአገር ውስጥ ማድረግ የሚያስችል ላቦራቶሪ ለመገንባት ለዓለም አቀፉ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ጽሕፈት ቤት(ዋዳ) የሚላኩ ቴክኒካል ሰነዶች እንደተዘጋጁም ጠቅሰዋል፡፡