አዲስ አበባ፣ ሰኔ 14፣ 2015(ኤፍ ቢ ሲ) የናይጄሪያ ብሔራዊ አየር መንገድን በጥቂት ወራት ውስጥ በማቋቋም ወደ ስራ ለማስገባት የሚያስችሉ የዝግጅት ስራዎች እየተጠናቀቁ መሆኑን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ፡፡
የናይጄሪያ ብሔራዊ አየር መንገድ ሲቋቋም የኢትዮጵያ አየር መንገድ 49 በመቶ ድርሻ እንደሚይዝ ይታወቃል፡፡
5 በመቶውን የናይጄሪያ መንግስት እንዲሁም የተቀረውን 46 በመቶ ደግሞ ሦስት የናይጄሪያ ባለሃብቶች እንደሚጋሩት ተጠቁሟል።
አቶ መስፍን ጣሰው ለኢዜአ እንደገለጹት÷ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት አየር መንገዶችን ሙሉ በሙሉና በከፊል የማስተዳደር ስራውን እውን እያደረገ ነው፡፡
የናይጀሪያ ብሔራዊ አየር መንገድን ለማቋቋም ስምምነት ላይ መደረሱን ተከትሎም የተለያዩ የዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅትም አየር መንገዱን ለማቋቋም ከናይጀሪያ መንግስትና ባለድርሻ ከሆኑ የናይጀሪያ ባለሃብቶች ጋር ሰፊ ውይይት በማድረግ ስምምነቶች መፈረማቸውን አረጋግጠዋል፡፡
ከናይጀሪያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ”የኤር ኦፕሬተር ሰርተፊኬት” ለመቀበል ሂደቶች መጀመራቸውንም ጠቁመዋል፡፡
እስከ መጪው ጥቅምት ወር የናይጀሪያ ብሔራዊ አየር መንገድ ተቋቁሞ በረራ እንዲጀምር እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቶጎ “አስካይ አየር መንገድ”፣ ”ከማላዊ አየር መንገድ ” እንዲሁም “ከዛምቢያ ኤር ወይስ” ጋር በጋራ እየሰራ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል፡፡
በተጨማሪም አየር መገዱ ከኮንጎ አየር መንገድ ጋር የነበረውን ሽርክና መልሶ ለመጀመር ከኮንጎ መንግስት ጋር ንግግር እያደረገ ነው ብለዋል፡፡
የናይጄሪያ ብሔራዊ አየር መንገድ ወደ ስራ ሲገባም የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካን በአቬሽን ዘርፍ ለማስተሳሰር በሚያከናውነው ስራ ላይ ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥ ተናግረዋል፡፡
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!