Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በመድኃኒት ለማይታከም የሚጥል በሽታ ቀዶ ሕክምና በኢትዮጵያ ለመጀመር ስምምነት ላይ ተደረሰ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በመድኃኒት ለማይታከም የሚጥል በሽታ ቀዶ ሕክምና በኢትዮጵያ ለመጀመር ስምምነት ላይ መደረሱን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ሕክምናውን ከስልጠና ጋር ለማስጀመር በእስራኤል ሀገር የሚገኘው “ኢንፊ” ተቋም ከኢትዮ-ኢስታንቡል ጄነራል ሆስፒታል፣ ከጤና ሚኒስቴርና ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ጋር  ለመስራት ስምምነት ላይ መድረሱ ተገልጿል፡፡

የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ÷ የሕክምናው መጀመር ኢትዮጵያን “በኒውሮሞዱሌሽን” ሕክምና ዘርፍ አንድ እርምጃ ወደፊት ያራምዳል ብለዋል፡፡

ለሕክምናው ባለሙያዎችን በማሰልጠንና በምርምር ከአዲስ አበባ ዪኒቨርሲቲ የሕክምና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ጋር በጥምረት እንደሚሰሩ ጠቁመዋል፡፡

እንደነዚህ ያሉ ስፔሻላይዝድ ሕክምናዎችን በማስጀመር የዜጎችን እንግልት ለማስቀረት እንደሚሰሩ የኢትዮ-ኢስታንቡል ጄነራል ሆስፒታል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ብርሀን አረተጋግጠዋል፡፡

የኢንፊ  ተቋም ተወካይ ዶ/ር ሚካኤል ሌቪ በበኩላቸው በእስራኤል ሀገር ሕክምናውን እየሰጡ መሆኖቸውን ጠቁመው÷ እስከአሁንም በርካታ ስኬታማ ቀዶ ሕክምና ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ሕክምናው በኢትዮጵያ ሲጀመር ከ5 እስከ 60 ዓመት ለሆናቸው ወገኖች አገልግሎቱ እንደሚሰጥ ተመላክቷል፡፡

በኢትዮጵያ ከሚገኙ የሚጥል በሽታ ታማሚዎች 70 በመቶ ያህሉ በመድኃኒት ሕክምና የማይድን በመሆኑ የቀዶ ጥገና ሕክምናው ያስፈልጋቸዋል  መባሉን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡

በኢትዮጵያ የሚጀመረው ሕክምና በመድሐኒት ለማይድን የሚጥል በሽታ ሕክምና የአፍሪካ ማዕከል እንዲሆን የሚያስችል መሆኑን  የኢንፊ ተቋም ኔውሮሎጂካል ኤክስፐርት ዶ/ር ጄሁዳ ሴፕከርት አስረድተዋል፡፡

የሚጥል በሽታ ቀዶ ሕክምናውን በቀጣዩ አመት በጥር ወር ለመጀመር እቅድ  ተይዟል፡፡

ከሚጥል በሽታ በተጨማሪ እንደ ፓርኪንሰን ያሉ የነርቭ በሽታዎች ሕክምናም ይሰጣልም ነው የተባለው፡፡

Exit mobile version