ቢዝነስ

ዓለም አቀፉ የዓየር የትራንስፖርት ማኅበር ጉባኤ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ነው

By Amele Demsew

June 20, 2023

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም አቀፉ የዓየር የትራንስፖርት ማኅበር (አያታ) በአፍሪካ ላይ ያተኮረውን ጉባዔውን ዛሬ በአዲስ አበባ ማካሄድ ጀምሯል።

“የአቪዬሽን ዘርፉን አቅም መጠቀም” በሚል መሪ ሐሳብ የሚካሄደው ጉባዔ÷ በአፍሪካ አቪዬሽን ዘርፍ ያሉ እድሎች እና ፈተናዎች ላይ እንደሚመክር ይጠበቃል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በጉባዔው ላይ የዓለም አቀፉ የዓየር የትራንስፖርት ማኅበር ዋና ዳይሬክተር ዊሊ ዋልሽ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው፣ የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ደንጌ ቦሩ፣ የአፍሪካ አየር መንገዶች ዋና ስራ አስፈጻሚዎች፣ የአቪዬሽን ዘርፍ መሪዎች እና ውሳኔ ሰጪዎችን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡

ለሁለት ቀናት በሚቆየው ጉባዔ÷ በአፍሪካ የአቪዬሽን ዘርፍ ደኅንነት በማሻሻል፣ አዋጪ የሕግ ማዕቀፎች በማዘጋጀት፣ የአየር ትስስርን በማጠናከርና የዘመነ የአየር መንገዶች የገበያ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ውይይት እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡

እንዲሁም መሰረተ ልማት እና አቅም ግንባታ፣ የሰለጠነ ሰው ኃይል ማፍራት እና ሌሎች በዘርፉ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች በጉባዔው ውይይት የሚደረግባቸው አጀንዳዎች ናቸው፡፡