ቢዝነስ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአሜሪካ አገልግሎት የጀመረበትን 25ኛ ዓመት አከበረ

By ዮሐንስ ደርበው

June 19, 2023

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አሜሪካ በረራ የጀመረበትን 25ኛ ዓመት አከበረ፡፡

በአሁኑ ወቅት አየር መንገዱ በዓለምአቀፍ ደረጃ ያለው ታዋቂነት እጅግ እያደገ የመጣ ሲሆን÷ በአፍሪካ ደግሞ ግዙፉ አየር መንገድ መሆኑ ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካን በአትላንቲክ አቋርጦ ከአሜሪካ ዋሺንግተን ዲሲ ጋር በበረራዎቹ ማገናኘት የጀመረው በፈረንጆቹ ሠኔ ወር 1998 ዓ.ም መሆኑን አየር መንገዱ በመረጃው አመላክቷል፡፡

የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አሥፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው በዓሉን በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክት ÷ በአሜሪካ አገልግሎት የጀመርንበትን 25ኛ ዓመት በተሳካ ሁኔታ በማክበራችን ደስ ብሎናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የወጪ ንግድን በማሳለጥ እና የሀገሪቷን ቱሪዝም በማስተዋወቅ ረገድ ትልቅ አስተዋፅዖ ማበርከቱን አስገንዝበዋል፡፡

በአፍሪካ እና አሜሪካ መካከል ያለውን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት በማጠናከር ረገድም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከፍተኛ ሚና መጫወቱን አስረድተዋል፡፡

አሁን ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አሜሪካን ከአፍሪካ ከተሞች አዲስ አበባ፣ ሎሜ እና አቢጃን ጋር በቀጥታ እያገናኘ መሆኑንም ተጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለፉት 75 ዓመታት ከአሜሪካ ጋር በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ተመሥርቶ ለዘለቀው ጉዞው የአሜሪካ መንግስትን እና የአቪዬሽን አጋሮቹን አመስግኗል፡፡

ዋና ሥራአስፈጻሚው አክለውም÷ አሜሪካ ሁሌም የስትራቴጂያዊ ዕቅዶቻችን ዋና አጋር እና ወሳኝ አካል ሆና ትቀጥላለች ብለዋል፡፡

የአፍሪካን እና የአሜሪካን ትብብር ይበልጥ ለማሳደግ እንጥራለን ያሉት አቶ መስፍን÷ በገበያ በማስተሳሰር ሁለቱን አኅጉራት ማገናኘታችንንም እንቀጥላለን ሲሉ አረጋግጠዋል፡፡