ቢዝነስ

ብሪታንያ ኢትዮጵያን ጨምሮ 65 አዳጊ ሀገራትን ተጠቃሚ የሚያደርግ የንግድ ስልት ይፋ አደረገች

By Amele Demsew

June 19, 2023

አዲስ አበባ፣ሰኔ 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ብሪታንያ ኢትዮጵያን ጨምሮ 65 አዳጊ ሀገራትን ተጠቃሚ የሚያደርግ የንግድ ስልት ይፋ አድርጋለች ።

በኢትዮጵያ የንግድ ስልቱን የማስጀመሪያ መርሐ ግብር በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በመርሐ ግብሩ ንግግር ያደረጉት የብሪታንያ ዓለም አቀፍ ንግድ ሚኒስትር ኒገል ሀድልስቶን፥ ይህ አዲስ የንግድ ስልት ለአዳጊ ሀገራት የንግድ ቀረጥን የሚቀንስ ነው ብለዋል።

በዚህ የንግድ ማዕቀፍ ተጠቃሚ የሚሆኑት ኢትዮጵያን ጨምሮ 65 አዳጊ ሀገራት በጥቅል ወደ ብሪታንያ በየዓመቱ ከሚልኩት 20 ቢሊየን ፓውንድ የሚያወጣ ምርቶቻቸው ተጠቃሚ ይሆናሉም ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ስራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ በበኩላቸው፥ የንግድ ስርዓቱ በተለይ በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚመረቱ ምርቶች በቀላሉ ወደ ብሪታንያ ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜ፥ የንግድ ስልቱ የሁለትዮሽ የንግድ ትስስር በመፍጠር አምራች ኢንዱስትሪዎችን በማበረታታት ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት መፋጠን ጉልህ ሚና እንደሚጫወት አስረድተዋል።

የንግድ ስለቱ መጀመር ኢትዮጵያ ያሏትን ፀጋዎች በመጠቀም የምታመርታቸውን ምርቶች ለዓለም ከማስተዋወቁም በላይ የተጀመረውን የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ውጤታማ እንዲሆን ያደርጋል ያሉት ደግሞ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ሀሰን መሀመድ ናቸው።

በዚህ የንግድ ስልት ተጠቃሚ ከሚሆኑ 65 አዳጊ ሀገራት መካከል 37ቱ የአፍሪካ ሀገራት ሲሆኑ፥ 3 ነጥብ 3 ቢሊየን ያክል ሰዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በሳሙኤል ወርቃየሁ