የሀገር ውስጥ ዜና

“ፋይዘር” በኢትዮጵያ መድሐኒቶችን ያለትርፍ ማቅረብ በሚችልበት ሁኔታ ላይ ምክክር ተደረገ

By Alemayehu Geremew

June 16, 2023

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካው “ፋይዘር” የመድሐኒት እና የክትባት አምራች ኩባንያ በኢትዮጵያ ጥራት ያላቸው መድሐኒቶችን ያለትርፍ ማቅረብ በሚችልበት ሁኔታ ላይ ከአምባሳደር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር ኢ/ር) ጋር መከረ፡፡

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር ኢ/ር) ከፋይዘር ዓለም አቀፍ የአዳጊ ገበያዎች ፕሬዚዳንት ኒክ ላኖዊች ጋር መወያየታቸውን በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል፡፡

በውይይቱም ÷ የኩባንያው ሥራ አሥፈፃሚዎች ቡድን “ሥምምነት ለጤናማ ዓለም” በሚል ዓላማ ኢትዮጵያን ጨምሮ ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው 45 አዳጊ ሀገራት መድሐኒቶችን እና ክትባቶችን ያለትርፍ ለማቅረብ በሚችልበት ሁኔታ ላይ ለመምከር ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጣ ተገልጿል፡፡

አምባሳደር ስለሺ(ዶ/ር ኢ/ር) ÷ ትብብሩ የአዳጊ ሀገራቱ ዜጎች ከፍተኛ ጥራት እና ውጤታማ መድሐኒቶችን እንዲያገኙ ያግዛል ብለዋል።