Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በኢንተርኔት የታገዘና በቀጥታ ስርጭት የሚሳተፉበት የቨርቿል ሩጫ እየተዘጋጀ ነው

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 20፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በታዋቂ አትሌቶች መሪነት በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንን የሚያሳትፍ በኢንተርኔት የታገዘና በቀጥታ ቪዲዮ በመታገዝ የቨርቿል ሩጫ እየተዘጋጀ ነው።

ዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘው የታላቁ አፍሪካ ሩጫ አዘጋጅ በላከው መግለጫ÷ በብርቅዬ አትሌቶች መሪነት፣ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንን የሚያሳትፍ የቨርቿል ሩጫ አየተዘጋጀ ስለ መሆኑ አስታውቋል።

ዝግጅቱ አትሌቶች በየአሉበት ቦታ ሆነው፣ በቪዲዮ ተራ በተራ እየሮጡ ለውድድሩ በተዘጋጀ ዙም (Zoom) በተሰኘ መተግበሪያ ላይ በቀጥታ በማህበራዊ ሚዲያ ከተሳታፊዎች ጋር የሚሮጡበት ነው ብለዋል።

በዝግጅቱ ላይ ከሚሳተፉ አትሌቶች መካከል ደራርቱ ቱሉ፣ ቀነኔሳ በቀለ፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣ ገንዘቤ ዲባባ፣ ስለሺ ስህን፣ ፋጡማ ሮባ፣ ሚሊዮን ወልዴ እና እጅጋየሁ ዲባባ እንደሚገኙበት ተገልጿል።

የውድድሩ ዋና አዘጋጅ ዶክተር ጋሻው አብዛ ÷የኮቪድ 19 በሽታ በዓለም ዙሪያ ከፈጠረዉ የጤና ፈተና ጎን ለጎን፣ በተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ እያደረሰ ያለው ኢኮኖሚያዊ እና ስነ ልቦናዊ ጫና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል።

በአገር ውስጥም ሆነ በውጭው ዓለም ያሉ ኢትዮጵያዊያን በተለይ ደግሞ ወረርሽኙ በበረታባት አሜሪካና አውሮፓ የሚገኙ ኢትዮያዊያን ከተለመደው የአኗኗር ዘይቤ በወጣ ፣ ረዘም ላለ ጊዜ ቤት ውስጥ ለመቀመጥ በመገደዳቸው፣ ሥራ አንደ ወትሮው ወጥቶና ነፃ ሆኖ መስራት አለመቻላቸውን ገልፀዋል።

ይሄ ደግሞ በበርካቶች ላይ ስጋትና የአዕምሮ ጭንቀት በመፍጠር ላይ እንደሚገኝ የገለፁት ዶክተር ጋሻው ÷ ጫናውን በተወሰነ ደረጃ ለመቀየር የሚያግዝ በኢንተርኔት በቤትና ግቢ ውስጥ ሆነው የሚሮጡት የቨርቿል ሩጫ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

በፌስቡክ እና ዩቲዩብ ላይቭ ላይ ከተለያዩ የዓለም ክፍል ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ጋር በተመሳሳይ ሰዓት በአንድ ላይ የሚያሳትፍ፣ ሁሉን ኢትዮጵያዊ የሚያሰባስብ የሩጫ ወይም የሶምሶማ ዝግጅት መሆኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ቨርቿል በታላቁ ሩጫ በዲሲ አስተባባሪነት ቅዳሜ፣ ግንቦት 8 ላይ እንደሚካሄድም ነው የገለፁት።

ተሳታፊዎችም በቤት ውስጥ ወይም ግቢ ውስጥ፣ የመሮጫ ማሽን ያላቸው ደግሞ ማሽኑ ላይ ሆነዉ እየሮጡ በስልካቸው፣ በኮሚፒውተር ወይም ከቴሌቪዠን ጋር አገናኝተዉ አትሌቶችን እየተከተሉ የሚሳተፉበት ዝግጅት መሆኑን ጠቁመዋል።

በዙም (Zoom) መተግበሪያ ላይ በቀጥታ የሚሳተፉት ሰዎች ከሌሎች በየትኛውም የዓለም ክፍል ከሚኖር ኢትዮጵያዊያን ጋር እየተያዩና ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሆነው የሚካፈሉበት ውድድር ሲሆን፣ ይህ እድልም ቀድመው ለሚመዘገቡ 1 ሺህ የቴክኖሎጂው አቅም ለሚፈቅደው ሰዎች እንደሚቀርብ  ተናግረዋል።

ከዝግጅቱ የሚገኘው ገቢ በኮቪድ 19 ዙሪያ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚሰሩ ሁለት መንግስታዊ ያልሆኑና በኢትዮጵያዊያን የሚመሩ አነስተኛ ድርጅቶች የሚበረከት  መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!

https://t.me/fanatelevision

Exit mobile version