የሀገር ውስጥ ዜና

የአፍሪካ ሕብረት የሰላም ፈንድ ሴክሬታሪያትና የዓለም ምግብ ፕሮግራም በትብብር ለመስራት ተፈራረሙ

By Shambel Mihret

June 15, 2023

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ሕብረት የሰላም ፈንድ ሴክሬታሪያት እና የዓለም ምግብ ፕሮግራም በትብብር መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራርመዋል።

ስምምነቱን የአፍሪካ ሕብረት የሰላም ፈንድ ሴክሬታሪያት ዳይሬክተር ዳግማዊት ሞገስ እና የዓለም ምግብ ፕሮግራም የአፍሪካ ሕብረት ዓለም አቀፍ ቢሮ ዳይሬክተር ሀመድ ኑሩ (ዶ/ር) ፈርመውታል፡፡

ስምምነቱ ሁለቱ ተቋማት በሰላም እና ጸጥታ መስኮች ስትራቴጂካዊ ትብብር መፍጠር እንደሚያስችላቸው የአፍሪካ ሕብረት አስታውቋል።

የሰላም ፈንዱ አፍሪካ የራሷን የሰላም እና ደህንነት ጉዳዮች በራሷ የገንዘብ አቅም ለማንቀሳቀስ የሚያስችል እና በሰላም ትብብር ትግበራ ላይ ዘላቂ እና ውጤታማ ስራ ለማከናወን እንደሚያግዝ መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል፡፡