የሀገር ውስጥ ዜና

በኦሮሚያ ክልል ባለሃብቶች በኢንቨስትመንት ዘርፍ እንዲሰማሩ ምቹና ቀልጣፋ አሰራር መዘርጋቱ ተገለጸ

By Meseret Awoke

June 15, 2023

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 8፣ 2015(ኤፍ ቢ ሲ) ባለሃብቶች በኦሮሚያ ክልል ያለውን እምቅ ሀብት በመጠቀም በኢንቨስትመንት ዘርፉ እንዲሰማሩ ምቹና ቀልጣፋ አሰራር መዘርጋቱን የክልሉ ኢንቨስትመንት እና ኢንዱስትሪ ቢሮ አስታውቋል።

የቢሮው ኃላፊ አሕመድ እድሪስ እንደገለጹት ፥ የሰሜኑ ጦርነት በስምምነት ከተፈታ በኋላ የክልሉ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ መነቃቃት አሳይቷል ፡፡

በርካታ ባለሃብቶች በክልሉ ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎታቸው መጨመሩንም ነው የቢሮ ሃላፊው የተናገሩት።

በተያዘው በጀት ዓመት በክልሉ ከ3 ሺህ 600 በላይ ለሚሆኑ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን ገልጸው፥ ፈቃድ ያገኙ ባለሃብቶችም በግብርና፣ በአግሮ ኢንዱስትሪ፣ በማኑፋክቸሪንግና በአገልግሎት ዘርፍ የሚሰማሩ ናቸው ብለዋል፡፡

ባለሃብቶቹ በአጠቃላይ ከ186 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ማስመዝገባቸውን ጠቁመው ፥ ፕሮጀክቶቹ በሙሉ አቅማቸው ወደ ስራ ሲገቡ ከ679 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል የመፍጠር አቅም እንዳላቸው አንስተዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል በኢንቨስትመንት ዘርፍ ያለውን አሰራር ለማቀላጠፍ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር በኩል ኃላፊነት መወሰዱን ጠቁመዋል፡፡

አንድ ባለሃብት ወደ ሸገር ከተማ ለኢንቨስትመንት ሲመጣ በፍጥነት መሬት በመረከብ ወደ ትግበራ መግባት የሚችልበት አሠራር ተግባራዊ እንደተደረገ መናገራቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ፈቃድ ከተሰጣቸው ባለሃብቶች መካከል 92 የኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ጥያቄ ያቀረቡ፣ 1 ሺህ 502 ወደ ኢንቨስትመንት የተሸጋገሩ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች እና 1 ሺህ 680 የሀገር ውስጥና የዳያስፖራ ባለሃብቶች እንደሚገኙበት ጠቁመዋል።