አዲስ አበባ፣ ሰኔ 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የዩናይትድ ኪንግደም አካል በሆነችው ዌልስ ውስጥ በስኖዶኒያ ተራሮች ስር 419 ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ሆቴል የዓለማችን ከመሬት በታች ጥልቅ ሆቴል ተብሏል።
ሆቴሉ ከዚህ ቀደም ለማዕድን ማውጫነት ያሚያገለግል በነበረ ቦታ ላይ የተገነባ መሆኑ ነው የተጠቆመው፡፡
አራት ነጠላ አልጋ ቤቶች እና ባለ ሁለት አልጋ ክፍሎች፣ የመመገቢያ ቦታ እና የመጸዳጃ ቤት መገልገያዎችን ያቀፈ ይህ ሆቴል ጥልቅ እንቅልፍ መተኛት እንደሚያስችል ተነግሮለታል፡፡
ከመሬት በታች የማዕድን ማውጫ በነበረ ሥፍራ 419 ሜትር ርቀት ላይ የተከፈተው ይህ ሆቴል÷በዓለም ላይ ጥልቅ ሆቴል በሚል አገልግሎቶቹን እያስተዋወቀ ይገኛል ፡፡
ሆቴሉ ሌሊቱን ጥልቅ እንቅልፍ ተኝቶ ማሳለፍ ለሚፈልግ ሁነኛ ቦታ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን÷ ለአንድ ሌሊት አዳር እስከ 550 ፓወንድ ወይም 688 ዶላር እንደሚያስከፍል ተጠቁሟል፡፡
በማዕድን ማውጫው ሥፍራ ወደሚገኘው ማረፊያ ክፍል ለመድረስ በተራሮች መሀል 45 ደቂቃ እና በዋሻ ውስጥ በአሮጌ የሀዲድ መስመር ለአንድ ሰዓት አስቸጋሪውን መንገድ ቁልቁል መጓዝ እንደሚጠይቅ ነው የተገለጸው፡፡
በፈረንረጆቹ ሚያዚያ ወር “ጎ ቢሎው” በተሰኘ ኩባንያ የተከፈተው ሆቴሉ÷ የምርቃት ስነ-ስርዓቱ ከዋሻው ውጭ መካሄዱ ተገልጿል፡፡
ሆቴሉ በሳምንት አንዴ ቅዳሜ ምሽት ብቻ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆንም ተመላክቷል።
ወደ ሆቴሉ በማቅናት ቅዳሜ ምሽት ያልተለመደውንና ድፍረት የሚጠይቀውን አገልግሎት ለማግኘት ደንበኞች ከወዲሁ ቀጠሮ ማስያዝ መጀመራቸው ተነግሯል፡፡
ሆቴሉ÷’የከመሬት በታች ዓለም ጥልቅ ሆቴል’ የሚለውን ማዕረግ ከዚህ ቀደም ከመሬት በታች 508 ጫማ ወይም 154 ሜትር ርቀት ላይ ተገንብቶ ከሚገኘው በስዊድን ሳላ ሲልቨር ማዕድን ሥፍራ ከተገነባው ሆቴል መውሰዱን ኦዲቲ ሴንትራል ዘግቧል፡፡