አዲስ አበባ፣ ሰኔ 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካዊው ተመራማሪ ጆሴፍ ዲቶሪ (ተ/ፕሮፌሰር) 100 ቀናት ባሕር ውስጥ በመኖር የዓለም ክብረ-ወሰንን ሰበሩ፡፡
እንደ ሲ ኤን ኤን ዘገባ÷ አዲስ የ“ጊነስ ወርልድ ሪከርድ” ያስመዘገቡት ተመራማሪው ምርምር ለማካሄድ በባሕር ውስጥ ቆይተዋል፡፡
በደቡብ ፍሎሪዳ ዩኒቨርሲቲ የባዮ ሜዲካል መምህሩ ጆሴፍ ዲቶሪ (ተ/ፕሮፌሰር) ÷ ምርምራቸውን የሠሩት በአሜሪካ በሚገኘው 6 ነጥብ 7 ሜትር ጥልቀት ባለው ኤመራልድ ሐይቅ ውስጥ በተገነባው “ጁልስ የባሕር ሎጅ” ላይ ነው፡፡
ሎጅው በአሜሪካ ብቸኛው የባሕር ውስጥ ሆቴል ተብሎም በሆቴሎች ድረ-ገፅ ዝርዝር ውስጥ መቀመጡ ተመልክቷል፡፡
ምርምሩ የባሕር ክብካቤ ላይ ያተኮረ ሲሆን÷ በተለይ በባሕር ውስጥ ያለው የውሃ ጫና እና ግፊት በሰው አካል ላይ በሚያሳድረው ተፅዕኖ ላይ ያተኮረ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
ከ100 ቀናት በኋላ የጆሴፍ ዲቶሪ (ተ/ፕሮፌሰር) ቁመት በ1 ነጥብ 27 ሴንቲ ሜትር መቀነሱም ነው የተገለጸው፡፡
የውሃ ግፊት የሰው ልጆች ረጅም ዕድሜ እንዲኖሩ እና ከእርጅና ጋር የተያያዙ በሽታዎችን እንዲቋቋሙ እንደሚያስችላቸውም በጥናቱ ተጠቁሟል፡፡
ጥናታቸው ለወጣቶች መነሳሳትን እና ለተለያዩ ሕመሞች ደግሞ ፈውስን ሊያስገኝ እንደሚችልም ያላቸውን ዕምነት ለ”ጊነስ ወርልድ ሪከርድስ” ተመራማሪው ተናግረዋል፡፡
ከዚህ በፊት “በጊነስ ወርልድ ሪከርድስ” የተመዘገበው ክብረ-ወሰን በተመሳሳይ ቦታ 73 ቀናት ከ 2 ሰዓት ከ 34 ደቂቃዎች መሆኑን የዓለም ክብረ-ወሰን መዝገብ መረጃ አስታውሷል፡፡