አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 3 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የግብርና ልማት ስራ የሁሉንም ህብረተሰብ ተሳትፎ የሚጠይቅ መሆኑን የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶር) ተናገሩ።
የ2015 ዓ.ም ሀገራዊ የመስኖ ስንዴ ልማት አፈፃፀም እና የ2015/16 ምርት ዘመን የመኸር እርሻ ልማት ዕቅድ እና ቅድመ ዝግጅት ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተካሂዷል፡፡
የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶር) በውይይት መድረኩ ላይ እንደተናገሩት÷ የግብርና ልማት ስራ የግብርናውን ዘርፍ ባለድርሻ አካላት ብቻ ሳይሆን የሁሉንም ህብረተሰብ ተሳትፎ የሚጠይቅ የልማት ስራ ነው ብለዋል፡፡
ባለፉት አመታት በመስኖ ስንዴ ልማት ላይ የታየውን የዘመቻ እና የቅንጅት ስራ በቀጣይ በሩዝ ልማት ላይ መድገም እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በቀጣይ የመኸር እርሻ ልማት ቅድመ ዘግጅት የኩታ-ገጠም እርሻ ስራን በማስፋፋት፣ በማሻሻል እና ከፍ በማድረግ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ይጠበቅብናል ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡
የእርሻና ሆርቲካልቸር ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን (ዶር) በበኩላቸው÷ በ2015 ዓ.ም 1 ነጥብ 3 ሚሊየን ሄክታር መሬት የመስኖ ስንዴን በማልማት 53 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማምረት ታቅዶ 1 ነጥብ 56 ሚሊየን ሄክታር በዘር በመሸፈን እስካሁን ባለው መረጃ መሰረትም ከተሰበሰበው ምርት ውስጥ 43 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል ምርት መገኘቱን ተናግረዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም በ2015 ዓ.ም በበልግ እርሻ 2 ነጥብ 48 ሚሊየን ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ 2 ነጥብ 58 ሚሊየን ሄክታር መሬት በዘር መሸፈን ተችሏል፡፡
በ2015/16 የምርት ዘመን በመኸር እርሻ 16 ነጥብ 6 ሚሊየን ሄክታር በማልማት 508 ነጥብ 7 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማግኘት የታቀደ ሲሆን 8 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር መሬት በኩታ-ገጠም እርሻ የሚለማ መሆኑን ዶክተር መለስ መናገራቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የክልሎች የ2015 ዓ.ም የመስኖ ስንዴ ልማት አፈፃፀም እና የ2015/16 የመኸር እርሻ ልማት ዕቅድ እና ቅድመ ዝግጅት እንዲሁም ወቅታዊ የግብርና ግብዓት አቅርቦትና ስርጭት ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡