ዓለምአቀፋዊ ዜና

ትራምፕ የአሜሪካን ከፍተኛ ሚስጥራዊ ሰነዶች በአግባቡ ባለመያዝ ክስ ቀረበባቸው

By Amare Asrat

June 10, 2023

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 3 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካን የኒውክሌር ሚስጥር እና ወታደራዊ ዕቅዶችን ጨምሮ በርካታ ሚስጥራዊ ሰነዶችን በአግባቡ አልያዙም በሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።

 

ትራምፕ ሚስጥራዊ ሰነዶችን ፍሎሪዳ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ‘የዳንስ ክፍል እና መታጠቢያ ቤት’ ውስጥ ደብቀው ማስቀመጣቸውም በቀረበባቸው ክስ ተጠቅሷል።

 

ከዚህ ጋር ተያይዞም ትራምፕ “መርማሪዎችን ዋሽተዋልም” ነው የተባለው።

 

በተጨማሪም ከሰነዶቹ አያያዝ ጋር በተገናኘ የሚደረገውን የምርመራ ሂደት ለማደናቀፍ ሞክረዋል በሚል ክስ እንደቀረበባቸውም ቢቢሲ ምንጮችን ዋቢ አድርጎ አስነብቧል።

 

በፈረንጆቹ 2024 ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የሚወዳደሩት ዶናልድ ትራምፕ ግን የቀረበባቸውን ክስ በማስተባበል ምንም ስህተት አልፈጸምኩም ብለዋል።

 

የህግ ባለሙያዎች ደግሞ ምናልባት ትራምፕ በቀረበባቸው ክስ ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ ከበድ ያለ የእስር ቅጣት እንደሚጠብቃቸው አስረድተዋል።

 

ባለ49 ገጹ 37 አይነት ትራምፕ ላይ የቀረበው ክስ፥ በአሜሪካ ታሪክ በፌደራሉ መንግስት በሀገሪቱ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ላይ የቀረበ የመጀመሪያው ክስ መሆኑም ነው የተገለጸው።