አዲስ አበባ፣ ሰኔ 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የፀረ ሽብር ወንጀል ምርመራ ዘርፍ በተጠረጠሩበት የሽብር ወንጀል ምርመራ ሲከናወንባቸው በቆዩ ተጠርጣሪዎች ላይ ነው ክስ የተመሰረተው።
ክሱን የመሰረተው የፍትህ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ ነው።
ክስ የተመሰረተባቸው ተጠርጣሪዎች ወንደሰን አሰፋ (ዶ/ር)፣ መስከረም አበራ፣ መሰረት ቀለመወርቅ (ዶ/ር)፣ ሲሳይ አውግቸው (ረ/ፕ)፣ ዳዊት በጋሻው፣ ገነት አስማማው፣ ጎበዜ ሲሳይ፣ መንበረ አለሙን ጨምሮ 24 ግለሰቦች ናቸው።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የፀረ ሽብር ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ክሱን ለመመልከት ተሰይሞ ነበር።
ይሁንና ከሳሽ ዐቃቤ ህግ ለችሎቱ ዳኞች ያቀረበው ክስ ለእያንዳንዱ ተከሳሽ የሚደርሰው ክስ ግን በችሎት ስነስርዓት መሰረት በሬጅስትራር አመሳክሮ ያላጠናቀቀና አንድ ማስረጃን አሟልቶ ያላቀረበ መሆኑን ተከትሎ ችሎቱ ተለዋጭ ቀጠሮ ለመስጠት ተገዷል።
በዚህም መሰረት አንዱ ማስረጃ ተሟልቶ ክሱ በሬጅስትራር ተመሳክሮ (ተረጋግጦ) ሲቀርብ ክሱን ለመመልከት ፍርድ ቤቱ ለፊታችን ሰኞ ሰኔ 5 ቀን ከሰዓት በኋላ ለመመልከት ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል።
በታሪክ አዱኛ