አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 30 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በተወዳዳሪ ነጋዴዎች እና ሸማቾች ላይ ጉዳት ያደረሱ ሁለት የንግድ ድርጅቶች ከ18 ሚሊየን ብር በላይ ቅጣት እንደተጣለባቸው የፍትሕ ሚኒስቴር አስታወቀ።
“ሁአሼንግ ኬብልስ” ማኑፋክቸሪንግ ኃ/የ/የግ/ማኅበር፥ ከደረጃ በታች የሆነ የኤሌክትሪክ ገመድ በማምረት እና ባመረተው ምርት ላይ ለተጠቃሚ የተዛባ መረጃ በመስጠት፣ በተወዳዳሪ ነጋዴ ላይ እንዲሁም በሸማቾች ላይ ጉዳት የሚያደርስ ተግባር በመፈፀሙ ቅጣት ተላልፎበታል።
በተመሳሳይም “ሰሂማ ጀማል ሰዒድ”፣ የተሰኘው ድርጅት ተመሳስሎ የተሠራ የውበት መጠበቂያ ምርት ከውጭ ሀገር አስገብቶ ገበያ ላይ በመሸጥ የተወዳዳሪ ነጋዴን የንግድ ጥቅም የሚጎዳ ተግባር በመፈፀሙ ችሎት ቀርቦ ተቀጥቷል።
ድርጅቶቹ ቅጣት የተጣለባቸው በንግድ እና ቀጠናዊ ትሥሥር ሚኒስቴር የንግድ ውድድር እና ሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 813/2006 አንቀጽ 8 ድንጋጌን ተላልፈው በመገኘታቸው መሆኑን የፍትሕ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ክሳቸው በችሎት ቀርቦ በክርክር ላይ የነበሩ ሲሆን፣ ችሎቱም ጉዳዩን በማስረጃ ካጣራ በኋላ ተከሳሾቹ ተገቢ ያልሆነ የንግድ ውድድር ተግባር መፈፃማቸው ተረጋግጦ በአዋጁ አንቀጽ 42/3 መሠረት ከዓመታዊ የሽያጭ ገቢያቸው ላይ 5 በመቶ እንዲቀጡ ውሳኔ አሳልፏል።
በውሳኔው መሠረትም፣ “ሁአሼንግ ኬብልስ” ማኑፋክቸሪንግ ኃ/የ/የግ/ማኅበር 17 ሚሊየን 733 ሺህ 946፣ “ሰሂማ ጀማል ሰዒድ” 424 ሺህ 370 ብር፥ በአጠቃላይ 18 ሚሊየን 158 ሺህ 317 ብር በቅጣት ለመንግሥት ገቢ ማድረጋቸውን የፍትሕ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!