አዲስ አበባ፣ ግንቦት 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ህገወጥ የሰዎች ዝውውር በህጋዊነት ተሸፍኖ እንዲካሄድ ደላሎች ከመንግስት ተቋማት ሰራተኞች ጋር እንደሚመሳጠሩ ታውቋል።
በድርጊቱም የትምህርት ምዘና ውጤትን ከሚሸጡ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት እስከ ስራና ክህሎት ሚኒስቴር ሰራተኞች ተሳታፊዎች መሆናቸውን ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በምርመራው ደርሶበታል፡፡
በዚህ ህገወጥነት ላይ ተጓዦች ሳይሰለጥኑና አስፈላጊውን ምዘና ሳያልፉ መረጃዎች የሚዘጋጅላቸው ሲሆን ለዚህ ደግሞ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ተባባሪ መሆናቸው ነው የተረጋገጠው።
ፋና ባገኘው መረጃ መሰረት የብቃት ማረጋገጫ (ሲ ኦ ሲ) ውጤት በገንዘብ ይሸጣል፤ መረጃውም ላልሰለጠኑ ተላልፎ ይሰጣል።
የኢፌዴሪ ስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አሰገድ ጌታቸው ችግሩ ስር የሰደደና በሁሉም ክልሎች የሚንጸባረቅ ነው ይላሉ።
በሌላ በኩል የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሰራተኞች ቸል በማለትና የጥቅም ትስስር በመፍጠር ለህገወጥ ድርጊቱ ተባባሪ ይሆናሉ።
በአዲሱ የስራ ስምሪት አዋጅ መሰረት ለስራ ወደ ውጭ ሀገራት የሚሰማሩ ዜጎች ቅድመ ክፍያ መክፈል እንደሌለባቸው ቢደነገግም ይህን በተቃረነ ሁኔታ በህገወጥ መንገድ ክፍያ ይፈፀማል።
ለዚህ ደግሞ ኤጄንሲዎች ከደላሎች ጋር የገቡበት መመሳጠር ምክንያት ተደርጎ የሚነሳ ሲሆን ደላሎች ከተለያዩ ተቋማት ሰራተኞች ጋር በመመሳጠርና ሀሰተኛ መረጃዎችን በማዘጋጀት ተሳታፊዎች ናቸው።
ፋና ባገኘው መረጃ መሰረት ከክፍለ ሀገር ፓስፖርታቸውንና ገንዘብ ብቻ በመላክ ጉዳያቸውን በብር የሚያስፈፅሙ ዜጎች የህገወጥ አዘዋዋሪዎች ሰለባ ናቸው።
ሌላው የህገወጥ ድርጊቱ ተሳታፊዎች የኢሜግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ሰራተኞች ሲሆኑ በተለይም ድንበር ቁጥጥር ላይ ገንዘብ በመቀበል በአየር መንገድ ለሚያልፉት ተባባሪ ይሆናሉ።
በምርመራችንም የስራና ክህሎት ሚኒስቴርና የኢሜግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ሰራተኞች፥ ከህገወጥ ደላሎች ጋር በመመሳጠር እንደሚሰሩ ያገኘናቸው የሰነድና የጉዳቱ ሰለባ ባለታሪኮች ነግረውናል።
በጉዳዩ ላይ ተከታታይ ዘገባዎችን እያቀረበ የሚገኘው ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የምርመራ ውጤቱን በቀጣይ ዘገባዎች የሚያቀርብ ይሆናል።
በአፈወርቅ እያዩ