የሀገር ውስጥ ዜና

የአሶሳ -ዳለቲ -ካማሺ- ባሮዳ የመንገድ ፕሮጄክት በተያዘለት ጊዜ ባለመጠናቀቁ ለከፍተኛ ችግር ተጋልጠናል – ነዋሪዎች

By Tamrat Bishaw

June 07, 2023

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በፌደራል መንገዶች አስተዳደር የሚሰራው አሶሳ -ዳለቲ -ካማሺ- ባሮዳ የመንገድ ፕሮጄክት በተያዘለት ጊዜ ባለመጠናቀቁ ለማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውሶች ተጋልጠናል ሲሉ የክልሉ ነዋሪዎች ለፋና ብሮድካስቲን ኮርፖሬት ቅሬታቸውን ተናገሩ፡፡

በ2009 ዓ.ም. አጋማሽ ውል የተገባለት የመንገድ ፕሮጄክት በእጅጉ መዘግየቱን ነው ነዋሪዎቹ የሚናገሩት።

የተቋራጮች ከጅምሩ በፍጥነት ወደ ስራ አለመግባት እና ተከስቶ የነበረው የፀጥታ ችግር ለመዘግየቱ ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው ተብሏል፡፡

መንገዱ በሶስት ተቋራጮች የተጀመረ ሲሆን 191 ኪሎ ሜትር ርዝመት እንዳለው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንገድ ትራንስፖርት ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡

መንገዱ ወደ ከተሞቹ የሚደረገውን ጉዞ ከግማሽ ኪሎ ሜትር በላይ የሚቀንስ በመሆኑ ነዋሪው መጠናቀቂያውን በጉጉት ሲጠብቀው መቆየቱን የክልሉ መንገድ እና ትራንስፖርት ቢሮ የመንገድ ጥናት፣ ክትትልና ዲዛይን ኮንትራት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት አቶ በፍቃዱ ሴፍ ተናግረዋል፡፡

የፌደራል መንገዶች አስተዳደር የአሶሳ አካባቢ ፕሮጀክቶች ፅሕፈት ቤት ቡድን መሪ ተጠሪ አቶ ምንተስኖት ከበደ መንገዱ በሶስት ሎቶች ተከፍሎ ለሶስት ተቋራጮች የተሰጠ ደረጃ ሁለት የአስፋልት መንገድ መሆኑን ገልጸዋል።

ከአሶሳ- ዳለቲ በሰነአን ኮንስትራክሽን የሚገነባ ሲሆን÷ ከዳለቲ እስከ ካማሺ ድረስ ያለው ቀሪ የመንገዱ አካል ደግሞ በኢኒ ኮንስትራክሽ የተያዘ እንደሆነም ነው የገለፁት፡፡

ሌላኛውን በሎት ሶስት የሚገነባው ነቀምት -ሶጌ- ካማሺ መንገድን ውል የወሰደ ተቋራጭ ደግሞ አኪር ኮንስትራክሽን መሆኑ ተገልጿል፡፡

መንገዱ የክልሉን ሶስት ዞኖች በአስፋልት የሚያገናኝ እና 6 ወረዳዎችንም የሚያቋርጥ መሆኑን የገለፁት ተጠሪው፥ የግንባታው መዘግየት ተቋራጮች ቀድመው ወደ ስራ ያለመግባታቸው ያስከተለው ችግር መሆኑን አንስተዋል፡፡

በዚህም ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው አንስተው፥ በአካባቢው የፀጥታ ችግር መከሰቱ ደግሞ ህዝቡን ለእንግልት እና የግንባታ ግብአት ውድመትም ፈጥሯል ብለዋል፡፡

አሁን ላይ በክልሉ ያለው ሰላም አስተማማኝ በመሆኑ ግንባታውን ለማስቀጠል ከተቋራጮቹ ጋር ውይይት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

የመንገድ ግንባታ ግብአት እና የነዳጅ አቅርቦት ፈታኝ ሊሆን እንደሚችል ስጋት አለን ያሉት ተጠሪው÷ ችግሩ የሚቀረፍ ከሆነ በፍጥነት ማገባደድ እንደሚቻል ጠቅሰዋል፡፡

በማርታ ጌታቸው