Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የአፍሪካ ንግድና ኢንቨስትመንት ዓመታዊ ጉባኤ መካሄድ ጀመረ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 29 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካን የንግድ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ለማነቃቃት በሚያግዙ ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ላይ አተኩሮ ምክክር የሚካሄድበት የአፍሪካ ንግድና ኢንቨስትመንት ዓመታዊ ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀመረ።

በጉባኤው የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ሀሰን መሀመድ፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ እንዳለው መኮንን፣ የአፍሪካ ኢንቨስትመንት ማዕከል ስራ አስፈፃሚ አብዲናስር ተርኪ እና የሌሎችም የአፍሪካ ሀገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ሃላፊዎችና ተወካዮች ተገኝተዋል።

ኢትዮጵያ በንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ በግብርና፣ በማዕድን እና በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ያላት አቅምና መልካም እድሎችን በሚመለከት በጉባኤው የሚነሳ ይሆናል።

ከኢትዮጵያ ባለፈ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ያላቸው የንግድና ኢቨስትመንት እድልና ተግዳሮቶችን በሚመለከት የመነሻ ፅሁፎች ቀርበው ምክክር ይደረግበታል መባሉን ኢዜአ ዘግቧል።

የንግድ እና ኢንቨስትመንት ጉባኤውን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ የማዕድን ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ 2023፣ የሶማሌ ላንድ ባንክ እና በሌሎች የሀገር ውስጥና የአፍሪካ ሀገራት ተቋማትና ድርጅቶች በትብብር የተዘጋጀ መሆኑ ታውቋል።

Exit mobile version