አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ስዊድናዊው አጥቂ ዝላታን ኢብራሂሞቪች በ41 ዓመቱ ራሱን ከእግርኳስ ዓለም ራሱን አግሏል፡፡
ግዙፉ አጥቂ በማልሞ፣ አያክስ፣ ጁቬንቱስ፣ ኢንተርሚላን፣ ኤሲሚላን፣ ባርሴሎና፣ ማንቼስተር ዩናይትድ፣ ፓሪ ሴንት ዥርሜን እና ኤል ኤ ጋላክሲ ክለቦች ተጫውቶ አሳልፏል።
በእነዚህ ጊዜያት በ866 የክለብ ጨዋታዎች ላይ 511 ጎሎችን አስቆጥሯል፡፡
ዝላታን ትናንት ማታ ክለቡ ኤሲ ሚላን የአመቱን የመጨረሻ ጨዋታ በሳንሲሮ ባደረገበት ወቅት ከደጋፊዎች ድንቅ አሸኛኘት ተደርጎለታል፡፡
በደጋፊዎች የክብር ሽኝት ስሜታዊ ሆኖ የተስተዋለው ዝላታን “እኔ የምሰናበተው እግር ኳስን እንጂ እናንተን አይደለም” ብሏል።
የዝላታንን ስሜታዊነት የተመለከቱ መገናኛ ብዙሃን አንበሳው አለቀሰ የሚል ዘገባቸውን ይዘው ወጥተዋል፡፡
ዝላታን ለሃገሩ ስዊድን በ122 ጨዋታዎች 62 ጎሎችን በማስቆጠር የምንጊዜውም ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ነው።
በክለብ ደረጃ 5 የጣሊያን ሴ ሪ አ፣ አራት የፈረንሳይ ሊግ 1፣ ሁለት የኔዘርላንድስ ሊግ ኤር ዲቪዜ እንዲሁም ከባርሴሎና ጋር አንድ የላ ሊጋ ዋንጫዎችን አሳክቷል።
በተጨማሪም ከማንቼስተር ዩናይትድ ጋር የዩሮፓ ሊግን ሲያሸንፍ፥ የአውሮፓ ትልቁ የእግር ኳስ የውድድር መድረክ የሆነውን የቻምፒየንስ ሊግ ዋንጫን ግን ማሳካት አልቻለም።