Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናትን የሚዘክር ዐውደ ርዕይ ተከፈተ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) “ላሊበላ በእምነት የታነፀ” በሚል መሪ ሀሳብ የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናትን የሚዘክር የአርኪኦሎጂና የቨርቹዋል ሪያሊቲ የቋሚ ዐውደ ርዕይ በላሊበላ ከተማ ተከፍቷል።

የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት÷በቱሪስት መዳረሻ ታሪካዊ ቅርሶች ዙሪያ ዕሴት የሚጨምሩ ተግባራትን በማከናወን ተወዳዳሪ መዳረሻነትና ማህበራዊ አቀፍ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው፡፡

ከዚህ ቀደም በእንጦጦ ፓርክ የላሊበላ ቨርቹዋል ሪያሊታ ዐውደ ርዕይ ተከፍቶ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መጎብኝታቸውን አስታውሰው በላሊበላም ተመሳሳይ አውደ ርዕይ መከፈቱን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያን መስህቦች በተለያዩ አማራጮች የማልማት፣ የመጠበቅና የማስተዋወቅ ስራዎች በስፋት እየተከናወኑ መሆኑን ነው ሚኒስትር ዴኤታው የገለጹት፡፡

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር ሕይወት ኃይሉ በበኩላቸው÷ቅርሶች ታሪክን ለመዘከር፣ ተፈጥሮና አካባቢን ለመረዳት ቅርሶች የመረጃ ምንጭ በመሆንና የገቢ ምንጭነታቸው የማይተካ ሚና አላቸው ብለዋል።

በፈረንሳይ ልማት ኤጄንሲ ድጋፍ በ22 የትኩረት መስኮች ለይቶ የሚሰራው ‘የላሊበላ ዘላቂ ልማት’ ፕሮጀክት ትግበራም ጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናትን ዕድሳትና ጥገና እንዲሁም የቅርሶችን ጊዜያዊ መጠለያ የማንሳት ስራዎች በጥንቃቄ እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የፈረንሳይ ኤምባሲ ተወካይና የኤምባሲው የባህል ካውንስለር ሶፊ ማካሜ ÷ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ የዘለቀው የኢትዮ ፈረንሳይ ወዳጅነትና ትብብር በታሪካዊ ቅርሶች ዘርፍ ቅድሚያ በመስጠት ተጨባጭ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል።

በላሊበላ ዘላቂ ፕሮጀክት ቅርሱን ለትውልድ ለማሻገር በሚደረገው ጥረት ፈረንሳይ የድርሻዋን እያበረከተች እንደሆነም መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

Exit mobile version