ስፓርት

ፊፋ የ150 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ለአባል ሀገራቱ ሊያደርግ ነው

By Meseret Awoke

April 26, 2020

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 18፣ 2012(ኤፍ ቢ ሲ)ፊፋ በኮሮና ቫይረስ ተጽዕኖ መቋቋሚያ የሚሆን የ150 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ለአባል ሀገራቱ ሊያደርግ ነው፡፡

የአለም አቀፉ እግር ኳስ አስተዳዳሪ አካል (ፊፋ) አባል ሀገራቱ በኮሮና ቫይረስ ከደረሰባቸው የፋይናንስ ተፅዕኖ እንዲወጡ የ150 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡

የፊፋ አባል ሀገራት በወረርሺኙ ምክንያት የፋይናንስ ችግር ውስጥ መግባታቸው ገልጾ በመጀመሪያው ዙር የሚደረገው የ150 ሚሊዮን ዶላር የእፎይታ ድጋፉ ለ211 የፊፋ አባል ሀገራት የሚደርስ ይሆናል፡፡

በመሆኑም እያንዳንዳቸው የፊፋ አባል ሀገራት 500 ሺህ ዶላር የሚያገኙ ይሆናል፡፡

የፊፋው ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ፤በወረርሽኙ ምክንያት ሊጎች እና ውድድሮች መቋረጣቸው ተከትሎ የእግር ኳስ ማህበራት ለከፍተኛ የበጀት ጉድለት ተዳርገዋል ብለዋል፡፡

በርካታ ክለቦችም ገቢያቸው በመቀነሱ ለተጫዋቾች እና ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞቻቸው ደሞዝ ለመክፈል መቸገራቸው የሚታወቅ ነው ፡፡

ኮሮና ቫይረስ ባደረሰባቸው ከፍተኛ የፋይናንስ ችግር አንዳንድ ክለቦች ተጫዋቾቻቸው የደሞዝ ቅነሳ እንዲያደርጉ በማግባባት ላይ ይገኛሉ ነው የተባለው፡፡

የፊፋው ፕሬዚዳንት ተቋማቸው ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ወደፊትም ድጋፉን እንደሚቀጥል መናገራቸውን ፊፋን ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል፡፡