የሀገር ውስጥ ዜና

ከ87 ሺህ በላይ አባወራዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የ30 ሚሊየን ዶላር ስምምነት ተፈረመ

By Shambel Mihret

June 02, 2023

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ87 ሺህ በላይ አባወራዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የ30 ሚሊየን ዶላር ስምምነት በፋርም አፍሪካ ኢትዮጵያና በኢትዮጵያ የስዊዲን ኤምባሲ መካከል ተፈረመ፡፡

ስምምነቱ በኢትዮጵያ ለሶስት ዓመታት የሚተገበር፣ ተፈጥሮን መሰረት ያደረገ ዘላቂ እና ሁሉን አቀፍ ልማት ላይ ያተኮረ ነው ተብሏል፡፡

ፕሮግራሙ በግብርና ሚኒስቴርና በፕላንና ልማት ሚኒስቴር ድጋፍና ክትትል የሚደረግበት ሲሆን÷ ፕሮጀክቱ 87 ሺህ 400 አባወራዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ይሆናልም ነው የተባለው፡፡

በኢትዮጵያ 5 ክልሎችና 35 ወረዳዎችን ተደራሽ እንደሚያደርግ መገለጹንም የፕላንና ልማት ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

የማህበረሰብ አቀፍ አደረጃጀቶች፣ አነስተኛ አርሶ አደሮች፣ ስራ ፈጣሪዎችና አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ከተጠቃሚዎች መካከል ይገኙበታል ተብሏል፡፡

መርሐ ግብሩ የሚተገበረው በስድስት የኢትዮጵያ ተፋሰሶች በሶስት የስነምህዳር ክላስተሮች መሆኑም ተገልጿል፡፡

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዲዔታ ሳንዶካን ደበበ÷የአየር ንብረት ለውጥና የአካባቢ ጥበቃ ስራን በተመለከተ በሀገሪቱ ለሚሰሩ ስራዎች ስምምነቱ ፋይዳ እንዳለው ጠቅሰዋል፡፡

የግብርና ሚኒስትር ዴዔታ ኢያሱ ኤሊያስ (ፕ/ር) በበኩላቸው÷የመሬት አሲዳማነትና መራቆትን መከላከል የተፋሰስ ልማትና የግብርና እሴት ሰንሰለትን ማዘመን ከፕሮጀክቱ የሚጠበቅ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የፋርም አፍሪካ ኢትዮጵያ ዳይሬክተር ወይዘሮ ሸዊት ኢማኑኤል÷ተቋማቸው ለፕሮጀክቱ ውጤታማነት ከፕላንና ልማት እንዲሁም ከግብርና ሚኒስቴር ጋር እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡

የስዊዲን መንግስት ለኢትዮጵያ የሚያደርውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጹት ደግሞ÷በኢትዮጵያ የስዊዲን አምባሳደር ሃንስ ሄነሪክ ሌንዲኩዊስት ናቸው፡፡