Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በኢትዮጵያ ለሚገኙ ለ189 ሺህ ስደተኞች ድጋፍ የሚውል 25 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ተጠየቀ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 25 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት (አይ.ኦ.ኤም) የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ለ189 ሺህ የኢትዮጵያ እና የሌሎች አጎራባች ሀገራት ስደተኞች ድጋፍ የሚውል 25ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ጠየቀ፡፡

በቀጠናው የተከሰተው ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲሰደዱ ምክንያትመሆኑንም ድርጅቱ አስታውቋል፡፡

ጦርነቱ በፈጠረው ቀውስ ለስደት የተጋለጡት ሰዎች ለጤና መቃወስ ፣ለሞት፣ለምግብ እጥረትና ለሌሎች በርካታ ችግሮች እንዲጋለጡ  እንዳደረጋቸው  የገለጸው ድርጅቱ  ይህንን ችግር ለመፍታት 25 ሚሊየን ዶላር እንደሚያስፈልግ ገልጿል፡፡

ካለፈው ወር አጋማሽ ጀምሮ ከ23 ሺህ በላይ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና የጎረቤት ሀገር ስደተኞች በመተማ መጠለያ ጣቢያ እንደሚገኙም አስታውቋል።

ከዚህ ባለፈም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኩርሙክ የመጠለያ ጣቢያ ወደ 800 የሚጠጉ ስደተኞች መኖራቸውን የጠቆመው ድርጅቱ፥ በመጭዎቹ ወራት የኢትዮጵያውያን ተፈናቃዮች ቁጥር 100 ሺህ እንዲሁም የጎረቤት ሀገራት ስደተኞች ቁጥር 30 ሺህ ሊደርስ እንደሚችልም ነው የገለጸው።

የተጠየቀው ገንዘብ በመጭዎቹ ስድስት ወራት ተጋላጭ ለሆኑ ስደተኞች እና ተፈናቃዮች ሰብአዊ ድጋፍ ለማድረስ የሚል መሆኑንም የድርጅቱ መረጃ ያመላክታል።

Exit mobile version