የሀገር ውስጥ ዜና

ተደራራቢ ግብርን ለማስቀረትና በታክስ ላይ የሚፈጸመውን ማጭበርበር ለመካለከል የቀረበው አዋጅ ጸደቀ

By Shambel Mihret

May 30, 2023

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተደራራቢ ግብርን ለማስቀረት እና በታክስ ላይ የሚፈጸመውን ማጭበርበር ለመከላከል የቀረበውን አዋጅ አጸደቀ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 23ኛ መደበኛ ስብሰባውን በማካሄድ ላይ ይገኛል።

ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ፣ስዊዘርላንድ እና በግራንድ ዱቺ ኦፍ ሉዘምበርግ መንግስት መካከል በገቢ ላይ የሚከፈለውን ግብር በሚመለከት በቀረበ ረቂቅ አዋጅ ዙሪያ መክሯል፡፡

በሀገራቱ መካከል ተደራራቢ ግብርን ለማስቀረት እና በታክስ ላይ የሚፈጸምን ማጭበርበር ለመከላከል የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ አስመልክቶ የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያቀረበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ አዋጁን አጽድቋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ከገንዘብ ሚኒስቴር የሕግ አማካሪ በተለያዩ መድረኮች በረቂቅ አዋጁ አስፈላጊነት ላይ እንደተወያየም የምክር ቤቱ መረጃ ያመላክታል፡፡

የምክር ቤቱ አባላትም÷ረቂቅ አዋጁ በታክስ ማጭበርበር የሚታዩ ግድፈቶችን ለማረም የሚያስችል እና የሀገራቱን ግንኙነት የሚያጠናክር አዋጅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡