አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በዋሽንግተን እና አካባቢው ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ጋር ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ።
ከንቲባዋ በዩናይትድ ስቴትስ የተለያዩ አካባቢዎች ያደረጉትን ጉብኝት አጠናቀዋል።
በዋሽንግተንና አካባቢው ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ጋር ባደረጉት ውይይ በአዲስ አበባ ስላለው የኢንቨስትመንት አማራጮች ጠቅለል ያለ መረጃም መሠጠቱን ገልፀዋል።
“በተለያዩ የሚዲያ አውታሮች ከሚሰሙት የተዛቡ መርጃዎች በላይ በከተማችን አዲስ አበባ ትላልቅ ሰው ተኮር ስራዎች እና ሜጋ ፕሮጀክቶች መሰራታቸውን ጠቅሰናል” ያሉት ከንቲባዋ፥ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያኑም ለመሳተፍ ያላቸውን ፍላጎት መግለፃቸውን ነው ያስታወቁት።
በውይይቶቹ ላይ ገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት የ200 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ ለማድረግና ፕሮጀክቶቹም ተገንብተው እስኪጠናቀቁ በቀጣይነት ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባታቸውን አመልክተዋል።
በአሜሪካ ለነበራቸው ቆይታ ስኬታማነት አስተዋፅኦ ለነበራቸው የኢትዮጵያ ኤምባሲ እና የዲያስፖራ አባላት ምስጋና አቅርበዋል።